ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፤ በከተማዋ ምሽት ላይ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው እና በተከለከሉ ሥፍራዎች ሲጋራ በሚያጨሱ ግለሰቦች እና በሚያስጨሱ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ማቀዱን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ እርምጃውን ለመውሰድ የተገደደው፤ በቀን የማይፈጸሙ ይህ ሕገ-ወጥ ድርጊት ጨለማን ተገን በማድረግ በምሽት እንደሚፈጸም የሚገልጽ ተደጋጋሚ ጥቆማ ከማኅበረሰቡ ስለደረሰ መሆኑ ተነግሯል።

Post image

በምሽት መዝናኛ ቦታዎች፣ በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ በህዝብ መመላለሻ ጎዳናዎች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በሆስፒታሎች እንዲሁም እና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ማናቸውም ቦታዎች ሲጋራ ማጨስ እንደማይፈቀድ፤ በባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው አስታውሰዋል።

"የትምባሆን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 11-12/2011 የሚተላለፉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አዋጁ የሚያስቀምጠው ቅጣት ይጣልባቸዋል" ብለዋል።

ጥፋተኞች ላይ እርምጃ የሚወሰደው ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ እና ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የቁጥጥር ሥራው በቀን ብቻ ሳይሆን ምሽትን ጨምሮ በበዓላት ቀናት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በተለይ ምሽት ላይ መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራት በብዛት እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

መሰል ተግባራትን የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ግለሰቦችና ተቋማትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዳይፈጸም የተከለከለውን ሲጋራ የማጨስ እና የማስጨስ ተግባር በምሽት ተቆጣጥሮ ጥፋተኞች ላይ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር በትክክል መቼ እንደሚጀመር አልተገለጸም።

ትምባሆ በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶችን ለጤና ችግር እያጋለጠ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ