በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የደቦ ፍርዶች፣ ግድያዎች፣ ብጥብጦች፣ ወንጀሎች፣ ዘረፋና መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መታየቱ የብዙዎችን ሥጋት አሳድሯል። በተለይ የፌዴራል መንግሥት፣ ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት የመከላከል ሥራ መሥራት ወይም ከተፈጸሙ በኋላ በፍጥነት እጁን በማስገባት የሕብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ያለመቻሉ ወቀሳና ትችት እያስነሳበት ይገኛል።

በሀገራችን የሕግ አፈጻጸም ጉድለት ቢኖርበትም፣ የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሕግና ሥርዓት የግድ አስፈላጊ መሆናቸው አያጠያይቅም። ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገራችን በአሉባልታ የሚመራ የደቦ ፍርድ ባሕል ገንኖ ወጥቶ የብዙዎችን ሕይወት ሲመሰቃቅል ተመልክተናል። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ መንግሥት የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያትም በዜጎች መካከል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶች የተወሰነ መብታቸውን ቆርጠው የሰጡት መንግሥት እንዲዳኛቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት በተሰጠው ሕጋዊ ሥልጣንና ኃይል በሚፈለገው ደረጃ ሕግ ማስከበር ካልቻለ፣ ከመንግሥት የበለጠ ለነፃነት አደገኛ የሆነ ሥርዓት አልበኝነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት አለ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አነሳሽነት የሚፈጸሙ ፍርዶች በሕግ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆኑ ይገለጻል። የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሣለኝ፣ እንዲህ ያለው ተግባር “በሕግ መርህ አስተሳሰብ የማይደገፍና ጸረ-ሕግ የሆነ ተግባር ነው” ሲሉ ይገልጹታል። ማንኛውም ፍርድ በፖሊስ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ፍርድ ቤት ሲፈርድበት ብቻ እንጂ በደቦ የሚደረግ ፍርድ ተገቢነት የለውም ይላሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ሰብዓዊ መብቶች የየዕለት ፍላጎቶቻችን” በሚል መሪ ቃል የሰብዓዊ መብት ቀንን እያከበረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑት የደቦ ፍርዶች እና ተጠርጣሪዎች ተገቢውን ከለላ ያለማግኘት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አንዱ ሆኖ ይገኛል። ይህንን በሚመለከት ሐሳባቸውን የሰጡት አቶ መብሪህ ብርሃኔ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የሕግ ባለሙያ ናቸው። እንደ እሳቸው ሐሳብ፣ ማንኛውም ሰው በሕግ ቁጥጥር ሲውል እንዴት ነው መያዝ ያለበት እንዲሁም እንደ ወንጀለኛ መያዝ እንደሌለበት ሕጉ ያስቀምጣል ይላሉ።

አቶ መብሪህ የሕግ አካላት ሕግን ብቻ መከተል አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎች ጫና ውስጥ ሊከቷቸው አይገባም ሲሉ ይገልጻሉ። ማኅበራዊ ሚዲያውን በርካቶች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እየተጠቀሙት ባለመሆኑ፣ ይህንን መቆጣጠርና አጥፊውን በአግባቡ መለየት ያለበት መንግሥት መሆኑን ያስረዳሉ። ሕጉ ግልጽ ሆኖ የተቀመጠ በመሆኑ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጸም የሚችሉ ድርጊቶችን መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

“መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ከሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚመጡት የዜጎችን የመኖር፣ የመሥራትና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቶች ይገኙበታል። ለዚህ እንቅፋት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ደግሞ ዜጎች በደቦ ፍርድ ምክንያት ሰብዓዊ መብታቸው እንዲገረሰስ መደረጉ ነው” ብለዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሣለኝ በበኩላቸው፣ “በአንድ ሀገር ውስጥ ለሚፈጸም ማንኛውም ወንጀል ተገቢውን ፍርድ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ብቻ ነው” ይላሉ። የሕግ የበላይነት ማረጋገጥም እንደሚያስፈልግ የገለጹት የሕግ ባለሙያው፣ በዚህ ውስጥ የሚገኙ አካላትም ወደ ፍርድ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ውዴታ እንጂ ግዴታ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታዩ ከባህልና ከሞራል አልፎም ከሕግ አግባብ ውጪ የሆኑ ጉዳዮችን ሥርዓት ማስያዝ የሕግ ሥልጣን መሆኑ ይታወቃል። ይህንን ለማድረግ ግን ሕግ በአግባቡ መተግበር ብሎም ሁሉንም በእኩል ማየት እንደሚያስፈልግ የሚገለጽ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ለመሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያው ወይም የደቦ ፍርዱ ለሕግ አካላት ግብዓት መሆን ይችላል ወይ ስንል የሕግ ባለሙያውን አቶ ካሳሁን ሙላትን ጠይቀናል። በምላሻቸውም ሕግን የማስከበርና ፍትሕን የማረጋገጥ ሥልጣን የሕግ ኃላፊነት ያለበት አካል እንጂ ማኅበራዊ ሚዲያው ወይም ሌላ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት መሆን የለባቸውም ብለዋል።

ሌላው በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረጉ ሁኔታዎችን በተመለከተ ፎቶ መለጠፍ አልፎም ሕግ ጥፋተኛ ሳይላቸው እንደ ጥፋተኛ የሚታዩበት ሁኔታ እንዴት ይታያል የሚለውም ጥያቄ ያስነሳል። ይህንን በሚመለከት አቶ ጥጋቡ ደሣለኝ ሲያሰረዱ፣ በሕጉ በግልጽ የተደነገገው ማዋከብ፣ ዘለፋ እንዲሁም ስድብ የመሳሰሉት መደረግ እንደሌለበት መደነገጉን ያነሳሉ። ይሁን እንጂ ፎቶ መለጠፍ ክፍት እንደሆነ የሚገልጹ ሲሆን፣ ይህ አካሄድ ሌሎች ዓለማት ላይም የሚደረግ መሆኑን ይናገራሉ።

ደቦ ፍርድ ላይ የሚሳተፉ አካላት ለፍርድ የሚቀርቡ መሆን አለባቸው የሚሉት አቶ ካሳሁን ሙላት፣ መንግሥት ይህንን የማስከበር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት ቀርቦ በዘፈቀደ መወሰን የለበትም ያሉም ሲሆን፣ የደቦ ፍርዱ በራሱ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

መንግሥት የደቦ ፍርዶችን መከላከል ብሎም በደቦ ፍርድ ውስጥ የተገኙ አካላትን ጭምር ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ይገለጻል። በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት መከበር ካለበት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ እርምጃዎች በሕግ አግባብም ሆነ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ተገቢውን ትኩረት መደረግ እንዳለባቸው ይነሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ