ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ግምታዊ ዋጋቸው ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶት እና አደንዛዥ እጾች እንዲሁም የአደንዛዥ እጽ መጠቀሚያዎች በመኖሪያ ቤት ውስጥ ተከማችተው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታውቋል።
180 ካርቶን ትምባሆ እና ከ600 በላይ ሺሻ ማስጨሻ እቃዎችን ጨምሮ 1 ሺሕ 276 ኪ.ግ. የሚመዝኑ የተለያዩ መድኃኒቶች እንዲሁም አነቃቂ እና አደንዛዥ እጾች በቁጥጥር ሥር የዋሉት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዓለም ባንክ አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደሆነ ተነግሯል።
የባለሥልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ገልገሎ ወልተጂ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት መድኃኒቶች እና እፆች በግለሰብ ቤት ውስጥ ለብክለት በሚያጋልጣቸው ቦታ ተቀምጠው እንደተገኙ አስረድተዋል።
የክፍለ ከተማው ኮማንድፖስት በአዲስ አበባ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን ከተቋቋመው ግብረ-ኃይል ጋር በመተባበር ባካሄዱት ክትትል በማኅበረሰቡ ጥቆማ የተያዘው ሕገ-ወጥ መድኃኒት እና እጽ እንዲወገድ መደረጉ ተነግሯል።
አቶ ገልገሎ አክለውም፤ ከውጭ ሀገራት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂ በመጠቀምም መድኃኒቱ በማን፣ የት፣ መቼ፣ እንዴት እንደተመረተ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘቱን እና አለማግኘቱን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጋር በመተባበር በግለሰቦች እጅ በአውሮፕላን የሚገቡ መድኃኒቶችን ለመቆጣጠር በቅንጅት የሚሰራበትን አሰራር መዘርጋቱም ተጠቁሟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ዋጋቸው ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች እና አደንዛዥ እጾች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ