ታህሳስ 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በአዲስ አበባ ከተማ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ከ434 ሺህ በላይ ደንብ የተላለፉ ተሽከርካሪዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ አስታውቋል።

ከዚህም ውስጥ ከ14 ሺሕ 600 በላይ የሚሆኑት ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር መከሰሳቸውን፤ በመምሪያው የትራፊክ ሙያና ሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

‎ከፍጥነት ወሰን በላይ ከማሽከርከር በተጨማሪም አልኮል ጠጥቶ በማሽከርከር ረገድ በ11 ሺሕ 400 አሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር፤ 172 አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

‎ከዚህ ባሻገርም ከ1 ሺሕ በላይ ያለ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ የተገኙ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ በተጨማሪ ከፍጥነት ወሰን በታች ያሽከረከሩ ከ500 በላይ አሽከርካሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል።

‎የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በቀዳሚነት የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሰጥ ያነሱት ዲቪዥን ኃላፊው፤ የሕግ መተላለፎች እንዳይከሰቱም ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

‎ለትራፊክ አደጋ መከሰት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ በመግለጽም፤ በተለይም ከፍጥነት ወሰን በላይ እና ጠጥቶ በማሽከርከር ላይ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

‎ዓመታዊ የቴክናክ ምርመራ በማያከናውኑት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዚህም ከ1 ሺሕ 700 በላይ አሽከርካሪዎች መገኘታቸውን እና ከ34 ሺሕ 800 በላይ አሽከርካሪዎች ደግሞ ቀይ የትራፊክ መብራት እንደጣሱ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ