ሕዳር 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ተጨማሪ ውይይት አይደረግም ሲል መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ "ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና እኩል አጠቃቀም በመሠረታዊ የዓለም አቀፍ ሕግ መርህ የሚመራ በመሆኑ ኢትዮጵያ በወሰኗ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም ከማንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ የለባትም" ሲል አስታውቋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለአሐዱ ሀሳባቸውን የሰጡት የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪ እና በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ተደራዳሪ የነበሩት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ "ግብፅ ማንኛውም አይነት ሀሳብ ብትሰጥ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብት አላት" ሲሉ ገልጸዋል።

ግብጽ 'ተጎድቻለሁ' የምትልበትን ጥያቄ በአግባቡ ለኢትዮጵያ አቅርባ መነጋገር ቢቻልም፤ ይህ መሆን አለመቻሉ የዲፕሎማሲያዊ ሽንፈቷን የሚጠቁም ነው ብለዋል።

አሁንም በሁለቱ ሀገራት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ከተፈለገ፤ የሁለቱም የጋራ እንቅስቃሴ የሚፈልግ እንጂ በኢትዮጵያ ይሁንታ የሚሆን አይደለም ባይ ናቸው።

ሌላው የቀድሞ ዲፕሎማት ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ ዲፕሎማሲ ሊኖራት እንደሚገባ አንስተዋል።

"የዲፕሎማሲ መርሆችን በተከተለ መንገድ አጀንዳ መቀበል ብቻ ሳይሆን አጀንዳ መስጠት አለባት" ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም እንደሀገር የነበረውን የዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መቀየርና ማሻሻል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ግብፅ 'ከዚህ በኋላ ለውይይት አልቀመጥም' ማለቷን እንደ ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት የሚታይ ነው ሲሉም አክለዋል። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በሁሉም መልኩ ያላትን ዝግጁነት ማጠናከር እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ