የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ 4 ወራት በተፈጸመ የመሠረተ ልማት ውድመትና የኃይል ስርቆት ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው እንደተገለጸው፣ በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትና በኃይል ስርቆት ውድመት ምክንያት ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል።
አገልግሎቱ እየደረሰ ያለው ስርቆት ከግለሰቦችና ከተቋማት አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን አስረድቷል። የትራንስፎርመር ስርቆት፣ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ ኬብል ስርቆት፣ በመኪና ግጭት የሚደርስ የመሠረተ ልማት ውድመት እንዲሁም የኃይል ስርቆት ለአገልግሎቱ ፈተና እንደሆነም ገልጿል።
በተለይም በ17 ትራንስፎርመሮች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ምክንያት 23 ሚሊዮን 85 ሺሕ 847 ብር የሚገመት ውድመት እንዳጋጠመው አገልግሎቱ በዛሬው ዕለት አብራርቷል። በአጠቃላይ በአራቱ ወራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በደረሰው ስርቆትና ውድመት፣ እንዲሁም በተፈጸመ የኃይል ስርቆት 143 ሚሊዮን 299 ሺሕ 114 ብር ተቋሙ ላይ ጉዳት አጋጥሟል።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር መግለጫው በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ 4 ወራት የተፈጸመ የመሠረተ ልማትና የኃይል ስርቆት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት አራት ወራት በ29 የኃይል ስርቆቶች ምክንያት 13 ሚሊዮን 184 ሺሕ ብር የሚበልጥ ጉዳት መድረሱን የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
“በአጠቃላይ በ4 ወራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በደረሰው ስርቆትና ውድመት፣ እንዲሁም በተፈፀመ የኃይል ስርቆት 143 ሚሊዮን ብር በተቋሙ ላይ ጉዳት እንደደረሰ” አቶ አንዋር ተናግረዋል።
በኃይል ስርቆት፣ በመሠረተ ልማት፣ በኬብል ስርቆት እና በመኪና ግጭት የተደረሱ ጉዳቶች ብዛት 107 መሆኑ ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ 10 የወንጀል ክሶች ተመስርተው ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በፖሊስ የምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊው “የዚህ መግለጫ ዋነኛ ዓላማ እነዚህ ስርቆቶች ሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንዲታወቅ መሆኑን” ዘርዝረዋል።
የተቋሙ የሕግና ሥነ-ምግባር ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተስፋ የመሠረተ ልማትና የኃይል ስርቆትን ለመከላከል የሚያግዙ ሕጎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የሕግ ክፍተት ሳይሆን በማስፈጸም በኩል ያሉ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል። የመሠረተ ልማት ጥበቃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍትሕ አካላትና ከሌሎች መስተዳድር አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
“ከኃይል ማመንጫ እስከ ተጠቃሚው ያለው መስመር ጥበቃና ሞግዚትነት የተቋሙ ኃላፊነት መሆኑን ያነሱት አቶ አበበ፣ ይህንን በተገቢው መንገድ መጠበቁን ማረጋገጥ ይገባናል” ብለዋል።
አቶ አበበ አክለውም፣ የመሠረተ ልማትና የኃይል ስርቆት ለኃይል መቆራረጥ ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ፣ ሕብረተሰቡ የተቋሙን መለያ ያላደረገ አካል የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን ሲነካካ ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።
በተጨማሪም “በ1997 ዓ.ም የወጣው በተለይም የቴሌ እና የመብራት ኃይል መስመሮችን ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ ማክበር ያስፈልጋል” ብለዋል። መሠረተ ልማቶቹ በተለያየ ክልሎችና ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ በመሆናቸው፣ በየደረጃው ያለ የአስተዳደር አካል ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም አስረድተዋል።
የተቋሙ የሕግና ሥነ-ምግባር ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተስፋ ሕግ ከማስከበር አኳያ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ያነሱ ሲሆን፣ ይህንን ለማስፈጸም ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የመሠረተ ልማት ጥበቃ ላይ የሚደርሱ ስርቆቶችን ለመከላከል፣ የመሠረተ ልማቶቹ በተለያዩ ቦታዎች እና ሰዎች የማይደርሱባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ መሆናቸው ፈተና መሆኑን ተናግረዋል። አጥፊዎችን ከተቋም ውስጥም ሆነ ከተቋም ውጪ ያሉትን ከወንጀል ተጠያቂነት በተጨማሪም ኤሌክትሪክ ኃይሉ እንዲቋረጥና የሰረቀው ኃይል በገንዘብ ተተምኖ እንዲከፍል እንደሚደረግም አንስተዋል።
“ሕግ ከማስከበር አኳያ ክፍተቶች እንዳሉበት ያነሱ ሲሆን፣ ይህንን ለማስፈፀም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል” ብለዋል።
በየክልል ከሚገኙ አስተዳደሮች ጋር በጋራ በመሆን ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ላይ እየሠሩ መሆናቸውን አቶ አበበ ተስፋ ጨምረው ተናግረዋል። በተለያዩ መድረኮችም በማዘጋጀት የመሠረተ ልማት ጥበቃ ላይ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
“በየክልል ከሚገኙ አስተዳደሮች ጋር በጋራ በመሆን ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ላይ እየሠሩ መሆናቸውን” ገልጸዋል።
የተቋሙ የማርኬቲንግ፣ ሽያጭና የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኦልጅራ የኃይል ስርቆትን ለመከላከል በተቋሙ አስተማሪ የቅጣት እርከኖችን ያካተተ መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በመመሪያው የኃይል ስርቆት የፈፀመ ደንበኛ ከ20 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጣ ገልፀው፣ ተጨማሪ ስርቆት ሲፈፀም ቅጣቱ እጥፍ እየሆነ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ከተቋሙ ሠራተኞች ውጪ ስርቆት የጠቆሙ አካላት የቅጣቱን 25 በመቶ እንደሚከፈላቸውም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
“በመመሪያው የኃይል ስርቆት የፈፀመ ደንበኛ ከ20 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ የሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጣ” ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 መሠረት፣ በኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም እስከ ብር 50 ሺሕ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው አቶ አንዋር አብራር፣ ከአገልግሎቱ ባለሙያዎች ጋር በተያያዘ በሚነሳ የሙስና እና የኃይል ስርቆት ጉዳይ ላይ መረጃዎች እየተጠናከሩ መሆኑንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉ አስረድተዋል።
“ከአገልግሎቱ ባለሙያዎች ጋር በተመለከተ በሚነሳ የሙስና እና የኃይል ስርቆት ጋር በተያያዘ መረጃዎች እየተጠናከሩ መሆኑንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉ” አስረድተዋል።
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋቋመበትን ዋነኛ ዓላማ በአግባቡ እንዳይወጣ ስርቆቱ ተጽዕኖ እያሳደረበት እንደሚገኝ ገልጿል። እንዲሁም፣ ሕብረተሰቡ አገልግሎቱን በሚፈልገው ደረጃ እንዳያገኝ ጫና በማሳደር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ሁሉም እንዲገነዘብ ሲል አስረድቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአራት ወራት ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ያስከተለው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት ጉዳይ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ኢኤአ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ 4 ወራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትና በኃይል ስርቆት ሳቢያ የደረሰውን እጅግ ከፍተኛ ኪሳራ ይፋ አድርጓል።