ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በኤች አይ ቪ/ኤድስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 601 ሺሕ 039 መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የስርጭት ምጣኔ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ከተመዘገበው በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑ በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት፣ በአዲስ አበባ ያለው የስርጭት መጠን 3 ነጥብ 14 በመቶ ሆኖ ሲገኝ፤ የሀገር አቀፉ ምጣኔ ደግሞ 0 ነጥብ 83 በመቶ እንደሆነ አስቀምጧል።
እ.ኤ.አ በ2024/2025 በጀት ዓመት አዲስ በኤች አይ ቪ ተይዘዋል ተብለው የተገመቱ ዜጎች ቁጥር 7 ሺሕ 962 ሲሆን፤ በየዓመቱ በአማካይ 9 ሺሕ 560 ሰዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተገልጿል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ጋር እንደሚኖሩ ከሚገመተው ሰዎች መካከል 94 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን አውቀው መድኃኒት እንደጀመሩ በጥናቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ከ0 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕጻናት 16 በመቶ፣ ከ15 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች 34 በመቶ እንዲሁም፤ 25 ዓመት እና ከዛ በላይ የሆኑ አዋቂዎች ደግሞ 51 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር ይሸፍናሉ።
በተለይም የአፍላና ወጣት ሴቶች የኤች አይ ቪ ስርጭት 1 ነጥብ 7 በመቶ እንደሆነ በጥናቱ ተረጋግጧል። በክልል ደረጃ ሲታይ ደግሞ፤ ከፍተኛው የኤች አይ ቪ ተጠቂዎች ቁጥር በቅደም ተከተል በአንደኛ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል ሲመዘገብ፣ ሁለተኛው ደግሞ በአማራ ክልል እንደሆነ ተገልጿል።
ማህበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ተማሚዎች እንዲገለሉ ያደርጋል" የተባለ ሲሆን፤ እራሳቸውን የሚያገሉ መኖራቸውም ነው የተነሳው፡፡ ቁጥሩ ሲታይም 38 መቶ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ይህ መረጃ ይፋ የሆነው፤ በዓለማቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ "ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ቃል ሕዳር 22 ቀን 2018 ዓም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በተከበረበት ወቅት ነው። የዚህ ዓመት የመሪ ቃል ትኩረት የመከላከል አቅምን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ "በተለይም በከተማ እና በገጠር የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ምጣኔ ይለያያል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል በሚሰራው ሥራ ውስጥ ከለጋሽ አካላት የሚለቀቀው ገንዘብ ማነስ ችግር እንደሆነና ሥራው ዘላቂነት እንዳይኖረው ማድረጉም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በተለይም ከመንግሥት ሠራተኞች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤድስ ፈንድ በማዋጣት በበሽታው ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት እና በበሽታው ጉዳት ለደረሰባቸው ሠራተኞች ድጋፍ ቢደረግም፤ "በኤድስ ፈንድ በየደረጃው የሚሰበሰበው ገንዘብ መጠን፣ ለምን ሥራ እንደዋለ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በወቅቱ መረጃ አለመሰብሰቡም ችግር ፈጥሯል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2010 የነበረባትን 1 ነጥብ 26 ከመቶ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አሁን ላይ ወደ 0 ነጥብ 85 ከመቶ ማድረስ ብትችልም አሁንም ቀሪ ሥራዎች ይጠብቁናል ሲሉም ሚኒስትር ደኤታው አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2030 ኤድስ የማኅበረሰብ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እየሠራች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ ዕቅድ እንዲሳካ ከተግዳሮቶች ጋር በመታገል የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምላሽን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ