ሕዳር 3/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ሜክሲኮ የሚገኘውን የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ የመጠቀም የ'ይገባኛል' መብት ጥያቄን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ እየተከራከረ እና ጉዳዩም በእግድ የተያዘ ቢሆንም፤ 'የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የራሱን ሠራተኞች አስተባብሮ ቢሮ ሰብሮ ቁሳቁሶቹን ወደ ውጪ ጥሏል' ሲል ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡

Post image

በ1939 ዓም የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ምክር ቤት ተብሎ በአዋጅ የተቋቋመው ምክር ቤቱ በ1957 ዓ.ም ከአባላት መዋጮ፣ መንግሥት በተከለለት በወጪ እና ገቢ እቃዎች ላይ በየዲክላራሲዮኖች ከሚለጠፍ የቴምብር ቀረጥ ሽያጭ 25 በመቶ እና ከኢትዮጵ ያንግድ ባንክ በተገኘ ብድር ባለ ሰባት ወለል ሕንጻ ግንባታው በ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የካቲት 23 ቀን 1957 ዓ፣ም መመረቁን የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ይሁን እንጂ በደርግ ዘመነ መንግሥት 1967 ዓም ሕንጻው በአዋጅ ሲወረስ የያዘውን የሕንጻ ወለሎች ይዞ ምክር ቤቱ ሲጠቀምበት እንደ ነበር፤ የምክር ቤቱ የአዲቮኬሲ እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ማሞ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በ2003 ዓም በወቅቱ በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ፊርማ እና ደብዳቤ ቀሪዎቹ የተወረሱት ወለሎች ሲመለሱ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባላደራነት (አስተባባሪነት) መላው የንግዱ ማህበረሰብ እንዲጠቀምበት ተብሎ እንደነበርም አቶ ካሳሁን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም "የሁለተኛ ወለል እና የምድር ወለል ይዘን ብንቆይም ቢሮውን እንድንለቅ ስንጠየቅ ተለዋጭ ቢሮ እንዲሰጠን በፍርድ ቤት ክርክር ጀምረናል" ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

"ከሁለት ወራት በፊት የጀመረው "ንብረት ይከበርልን" ጥያቄ መልስ ባላገኘበት እና የፍርድ ቤት እግዳ ባልተነሳበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ቢሮዎችን በመስበር እቃዎችን አውጥቶ ጥሏል" ሲሉም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

Post image

"የኛ ክርክር 'ቢሮውን አንለቅም' ሳይሆን ነገር ግን በፍርድ ቤት የተወሰነልን ውሳኔ ይከበር ነው" ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከመንግሥት ውርስ በፊትም ሆነ ከተመለሰ በኋላ የያዘውን ቢሮ ይዞ የመጠቀም መብቱ እንዲረጋገጥለትና ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲፈታ አቤቱታውን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ተመልክቶ ሕዳር 3 ቀን 2018ዓም እግድ አውጥቷል ተብሏል፡፡

Post image

"ነገር ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አላከበረም" ሲሉ የምክር ቤቱ የአዲቮኬሲ እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ማሞ ገልጸዋል፡፡

አሐዱም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ያናገረ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ "የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አልጣስኩም" ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሰብሳቢ አባ ሴራ አባ ጆብር፤ "የአዲስ አበበባ ንግድ ምክር ቤት የሚጠቀምበትን የሕንጻው የምድር ቤት ቢሮ እንዲለቅ የተጠየቀው ከአንድ ዓመት በፊት ነው" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

Post image

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የራሱን ሕንጻ የማልማት መብቱን በመጠቀም እና ከኮሪደር ልማቱ በኋላ መጀመሪያ ወለሎች ለቢሮ የማይፈቀድ በመሆኑ፤ የጨረሻው ወለል ላይ ያሉ ተከራዮችን ባንኮችን ጨምሮ አስወጥቷል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አክለውም "ለአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትም ተቀያሪ ሦስተኛ ወለል ላይ ቢሮ ሰጥተናል" ነው ያሉት፡፡

በዚህም "የሚገለገልባቸውን እቃዎች አውጥቷል" ያሉት ሰብሳቢው፤ "የማይገለገልባቸውን እቃዎች በጨረታ እስከሚያስወግድ ታሽገው እንዲቀመጡ ደብዳቤ ፅፎ ተፈቅዶለት ነበር፤ ነገር ግን እቃዎቹን ማውጣት ባለመቻሉ ቢሮው ተሰብሮ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መጋዘን እቃዎቹ እንዲሄዱ ተደርገዋል" በማለት የቢሮ መስበሩን ጉዳይ ሰብሳቢው አምነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በበኩሉ ምንም አይንት ተለዋጭ ቢሮ እንዳልተሰጠው እና ማስጠንቀቂያዎችም እንዳልደረሱት ነው ለአሐዱ የገለጸው፡፡ በዚህም ምክንያት የፍርድ ቤት ክርክሩ "ተለዋጭ ቢሮ ይሰጠኝ" መሆኑን አክሏል፡፡

Post image

የቂርቆስ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሄር ችሎት ሰኞ ሕዳር 1 ቀን 2018 ዓ/ም በሰጠው እና አሐዱ የተመለከተው ብይን መሠረት፤ ተከሳሽ ከሳሽ ይዟቸው የነበሩ ክፍሎችን ቢሮ ቁልፎች ሰብሮ ወደ ክፍሎቹ የገባ ከሆነ፤ ፍ/ቤቱ በሰጠው እግድ መሰረት በአስቸኳይ ክፍሎቹን ለከሣሽ እንዲያስረክብ እና ከሣሽ ትናንት ሕዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ላቀረበው 'የእግድ ተጣሰብኝ' አቤቱታ ምላሹን በቀጣይ ቀጠሮ በፅሁፍ እንዲቀርብ በጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ