ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 83 በመቶ አካባቢዎቹ ለወባ አጋላጭ በሆነው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ዳጋት ቀበሌ የተከሰተው የወባ በሽታ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ የክልሉ ነዋሪዎች ለአሐዱ ሬዲዮ ባሰሙት ቅሬታ ገልጸዋል።

ሙሉ የቤተሰብ አባላት በበሽታው በመያዛቸው አስታማሚ የተቸገሩ ነዋሪዎች እንዳሉ ያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለወባ ሕመምተኞች ይደረግ የነበረው ድጋፍ መቋረጡ "ችግሩን አባብሶታል" ብለዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ታማሚዎች የሕክምና እርዳታ ባለማግኘታቸው ሕይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ለአሐዱ ያብራሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በአካባቢው የሚገኘው 'አጣጥ ሆስፒታል' በአንድ የሆስፒታል የታካሚ አልጋ ላይ ሁለት ሕመምተኞች ለማስተኛት መገደዱን ገልጸዋል።

በቅሬታ መልክ ለቀረበው ክስተት ምላሽ እንዲሰጡ በአሐዱ የተጠየቁት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ገዙ፤ ያለፉት ሦስት እና አራት ወራት ለወባ መስፋፋት አመቺ የአየር ጠባይ እንዳላቸው ጠቅሰው የክልሉ ጤና ቢሮ ችግሩን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ያሉትን ሲጠቅሱም፤ "ከጤና ሚኒስቴር የምናገኘው የአጎበር እና የኬሚካል አቅርቦት በጠየቅነው እና በሚያስፈልገን ጊዜ አልደረሰልንም፤ ዘግይቶብናል" ብለዋል።

የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ከስርጭቱ ስፋት አንጻር ስርጭቱን በመከላከል ረገድ አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውን ያልሸሸጉት ኃላፊው፤ በክልሉ ከሚገኙ 82 ወረዳዎች መካከል 32 ያህሉ የኬሚካል ርጭት እንደተከናወነላቸውና በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ 18 ወረዳዎች ተለይተው የአጎበር ስርጭት እንደተካሄደ ገልጸዋል።

ቢሮው ከጤና ሚኒስቴር የጠየቀው ድጋፍ ሲደርስ ወረርሽኙን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንደሚቻልም አቶ ቢንያም ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ