ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እስከ 2030 ዓ.ም. የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት፤ ያያ የክፍያ ሥርዓቶች አክሲዮን ማህበር (ያያ ዋሌት) የተሰኘውን የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋም 12ኛ አጋር በማድረግ በዛሬው ዕለት ስምምነት ተፈራርሟል።

ይህ ስምምነት የጤና ተቋማት የክፍያ ዘርፍን ወደ ዲጂታል ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አማራጮችን በማስፋት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ ዘርፉ ለሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ክፍት እንደሆነ ገልጾ፤ የወጡትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ባንኮችን እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (ፊን-ቴክ) ተቋማትን እየተቀበለ ይገኛል።

የያያ ዋሌት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ በልሁ እንዳሉት፤ ተቋማቸው ከዚህ ቀደም ባለፉት 12 ወራት ከአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር በመሥራት በክፍያ ዘርፉ ላይ የሙከራ ጊዜውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል።

Post image

አቶ ዮሐንስ አክለውም፤ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በሚኖረው የሥራ ጊዜ በተለይ የክፍያ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያስፈልገው የአገልግሎት ክፍያ በውይይት ተወስኖ በሚቀመጥ የክፍያ መዋቅር ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል።

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ በተለይ ሆስፒታሎች እና ፋርማሲዎች ሁሉን አቀፍ በሆነ የክፍያ ሥርዓት እንዲታገዙ በማድረግ የጤና አገልግሎቶችን የበለጠ ለማቀላጠፍ ይረዳል ተብሏል።

በጤና ተቋማት የሚደረገውን የጥሬ ገንዘብ ክፍያ በማስቀረት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ለወረቀት የሚወጣውን ወጪ እንደሚቀንስ ተገልጿል።

Post image

ስምምነቱ ኤሌክትሮኒክ የታካሚ ምዝገባ (EMR) ለሌላቸው ተቋማት፤ ዲጂታል ክፍያዎችን ወዲያውኑ ለመቀበል እና ፋይናንስን ለማስተዳደር የሚያስችል፣ የጤና ተቋማት በሚፈልጉት መልኩ መሻሻል የሚችል ልዩና ገለልተኛ የዳሽ ቦርድ ሥርዓት (standalone dashboard system) የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ያያ የክፍያ ሥርዓት ከኢት-ስዊች ጋር ባደረገው ጥምረት ከመላው ሀገሪቱ ባንኮች እና ሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመገናኘት የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ