ሕዳር 4/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በያዝነው በጀት ዓመት የጀመረው እና ተግባራዊ ያደረገው በሞባይል መተግበሪያ የታገዘ ወረቀት አልባ የአሰራር ሥርዓት፤ የአበባና ፍራፍሬ አምራች ድርጅቶች ከዘርፉ እንዳይወጡና የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት ቀድሞ የወጡትም እንዲመለሱ የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ገልጿል።

ማኅበሩ ባለስልጣኑ ከ188 ሀገራት ጋር የፈጠረው የገበያ ትስስር እና ወረቀት አልባ ዲጂታል የአሰራር ሥርዓት በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ ተቋማት አበረታች ሆኗል ብሏል።

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ፤ "ምርት የመላክ ስርዓቱ ዲጅታላይዝድ መሆኑ ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያግዛል፡፡ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪም ያሳድጋል" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

Post image

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና አባል የሆነችው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥረት እያደረገች እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ አዲሱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ከእድሎቹ በስፋት እና በጥራት ለመጠቀም ምቹ መደላድል ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር፣ በዚህም የገበያ ተወዳዳሪነት እንዲፈጠር ያስችላል የተባለለት ዲጅታል የአሰራር ስርአት የግብርና ግብአት የሆኑ ምርቶች ከክልል በማንቀሳቀስ ሂደት ውስጥ የነበረውን ችግር እንደሚያስተካክል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍን በአሁኑ ወቅት በዓመት በአማካይ ከ500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን፤ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

Post image

ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. ወደ ውጪ ከሚላክ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት 564 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፤ በ2018 በጀት ዓመትም ገቢውን በማሳደግ 735 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ይህን እቅድ ለማሳካት እንዲሁም የወጪ እና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍና የኤክስፖርት ተወዳዳሪነትን ለመጨመር በማሰብ፤ (ኢ-ፋይቶ) 'Electronic Phytosanitary Certificate' የተሰኘ የዕፅዋት ንፅህና ማረጋገጫ ወረቀትን በኤሌክትሮኒክ መልክ የሚሰጥ ሥርዓት በተያዘው ዓመት ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ