ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እንደ ኮሊስትሮል፣ ጨው እና ስኳር ያሉ ቅመሞችን ጨምሮ ሌሎችንም ማጣፈጫዎች ከተቀመጠው ደረጃ በላይ የሚጠቀሙ የታሸጉ የፋብሪካ ምግብ ነክ ምርት አምራቾችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ፤ በምርቱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ወይም የተጎዳ ሰው በማስረጃነት እንዲቀርብ በፍርድ ቤቶች መጠየቁ አግባብነት እንደሌለው የአዲስ አበባ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
ድርጊቱ ከሰፊው ማኅበረሰብ ይልቅ ለአጥፊዎች ያደላ ውሳኔ እንዲተላለፍ ያደርጋል ተብሏል።
የባለሥልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው፤ ምርቶቹ እንደ ካንሰር፣ ስኳር፣ ደምግፊት፣ ከልክ በላይ ውፍረት እና ኩላሊት ላሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ቢሆኑም፤ የምርቶቹ ጉዳት በፍጥነት ስለማይታይ ሕይወቱ ያለፈን ወይም በተሳሳተ 'ፎርሙላ' በተዘጋጀው ምርት ምክንያት የጤና እክል የደረሰበትን ሰው በማስረጃነት ማቅረብ አይቻልም" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አቶ እስጢፋኖስ በተጨማሪም፤ "የምርቶቹ ለጤና ጎጂ መሆን በላቦራቶሪ ምርመራ ከተረጋገጠ እና ለማይድኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ መሆኑ በባለሙያዎች ከተመሰከረበት ፍርድ ቤቱ እንደ ተጨባጭ ማስረጃ ሊቆጥረው ይገባል" ብለዋል፡፡

በዚህም "ምርቶቹ ለበሽታ የሚያጋልጡት በረዥም ጊዜ መሆኑ እና ሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ ችግር አለማስከተላቸው ከሰው ምስክር ይልቅ የላብራቶሪ ምርመራን ለማስረጃ ማቅረብ የበለጠ አዋጭ ይሆናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ለበሽታ አጋላጭ የሆነ ምርት ሲያመርት የተደረሰበት ተቋም ወዲያውኑ በወንጀል ተጠያቂ መሆን እንደሚገባው የገለጹት ኃላፊው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታውን ያልተረዳ የፍርድ ቤቶች አሰራር ምክንያት ይህንን ለማድረግ መቸገራቸውን አንስተዋል።
በባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራ የንፅህና ጉድለት ሲገኝ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድና ለጤና አስጊ የሆኑ ኬሚካሎች ሲገኙ ደግሞ ምርቱ ተሰብስቦ እንደሚወገድም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በዚህም አምራች እና ሻጩን ከገበያ ትስስሩ ማስወጣት፣ የንግድ ፈቃድ መሰረዝ፣ ማገድ እና መሰል አስተዳደራዊ እርምጃዎች በተቋሙ በኩል የሚፈጸሙ አጥፊዎችን የመቅጫ መንገዶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ