ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አንጻር የአጥንት ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር 695 ብቻ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ስሌት መሠረት አንድ ባለሙያ 300 ሺሕ ሰው እንደሚያገለግል የኢትዮጵያ የአጥንት ሐኪሞችና ባለሙያዎች ማኅበር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በማገልገል ላይ ከሚገኙ 16 የውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር ሲደመር የባለሙያዎችን ቁጥር 711 ያደርሰዋል ተብሏል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤፍሬም ገብረሃና፤ "የኢትዮጵያውያን አጥንት ሕክምና ዶክተሮች ቁጥር 695 ቢሆንም፤ የስፔሻሊስቶቹ ቁጥር 400 ብቻ ነው" ብለዋል።
295 ሐኪሞች በዘርፉ ስፔሻላይዝድ ለማደረግ በመሰልጠን ላይ እንደሆኑ አንስተው፤ "የባለሙያዎቹ ቁጥር 120 ሚልዮን ለሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ሲካፈል አንድ ባለሙያ 300 ሺሕ ሰዎችን እንደሚያገለግል ያሳያል" ሲሉ አስረድተዋል።
ለባለሙያዎቹ ቁጥር ማነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል፤ በአጥንት ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ሥልጠና የሚሰጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር ማነስና ዘርፉ የሚጠይቀውን የመግቢያ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች አነስተኛ መሆን ይገኙበታል።
ማኅበሩ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዲሁም ከባሕላዊ የአጥንት ወጌሻ ባለሙያዎች እና ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
በተጨማሪም የአጥንት ሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመርም የራሱን ጥረት እንደሚያደርግ ማኅበሩ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ያለው የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ቁጥር ለ300 ሺሕ ሰዎች አንድ እንደሆነ ተገለጸ