ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከሰቱን በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡ ተከትሎ፤ እስካሁን በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሎ ምርመራ ከተደረገላቸው 73 ሰዎች ውስጥ 6ቱ ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ ያካተተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሽታ መከሰቱን በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡ መገለጹን አስታውሰው እስካሁንም ድረስ 73 የተጠረጠሩ ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህም 6ቱ ታማሚዎች ሕይወታቸው በቫይረሱ ያለፈ መሆኑን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ሪፈረንስ ላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሲሆን፤ አምስቱ ደግሞ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም እስካሁን 349 ሰዎች ንክኪ ያላቸው በመሆኑ ክትትል እየተደረገ ሲሆን፤ 119ኙ ደግሞ የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን በማቋቋምና የሰለጠነ የሰውሃይል እና አስፈላጊውን የሕክምና ግብአት በማደራጀት ለታማሚዎች የተጠናከረ የህክምና እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለታማሚዎችም የተሻለ ሕክምና ለመስጠት ይቻል ዘንድ ከዚህ በፊት ወረርሽኙ ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግና ልምድ በመቅሰም ከዚህ በፊት ተሞክረው ጥሩ ውጤት ያስገኙ መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በመለየትና ወደሃገር ውስጥ በማስገባት ለታካሚዎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ብለዋል ዶ/ር መቅደስ።
አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከተገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት፣ የሕክምና አቅርቦቶች እና የሰለጠኑ ሰራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ፤ ቫይረሱ ባልተገኘባቸው ክልሎችም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም መሠረት በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በድንበር ቦታዎች እና በሌሎች የመግቢያ እና የመውጫ ቦታዎች ላይም ምርመራው መጠናከሩን ተናግረዋል።
የበሽታውን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰዉ በሚመለከቱበት ጊዜ በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ ወይም በ8335 እና 952 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የተገለጸም ሲሆን፤ ስለበሽታው ተጨማሪ መረጃ እንዲሁም የምክር አገልግሎት ለማግኘትም እነዚህን የነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም እንደሚቻል ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ