ሕዳር 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃት አድራሽ ሰዎች ለሕጻናት አገልግሎት የሚሰጡባቸው የትኛውም ተቋም ውስጥ እንዳይሰሩ የሚያደርግ የምዝገባ ስርዓት ማዘጋጀቱን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕጻናት መብት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዘቢደር ቦጋለ፤ "ጥቃት አድራሾች ምዝገባ ስርዓት" ወይንም (Sex offender registration system) መፈጠሩን ገልጸዋል።

የዚህ ስርዓት አስተግባሪዎች የፍትሕ አካላት መሆናቸውን ገልጸው፤ አንድ ጥቃት አድራሽ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህም የሚሆነው የአጥፊም ሰነድ ተመዝግቦ አለመቀመጡ እንደሆነና ሕጻናት በሚኖሩባቸው የትኛውም ተቋማት ውስጥ እንዳይሰሩ ለማድረግ ምዝባው አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ስርዓቱ ወደ ትግበራ ሂደት እየተገባ መሆኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከዚህ ባሻገር ወጣቶች እና ሕጻናት ላይ ግንዛቤ የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በማህበረሰብ ውስጥ ጥቃት ተከላይ ግብረ ኃይሎች መፍጠር እና የተለያዩ ኮሚቴዎችን በመፍጠር፤ ስልጠናዎችን መስጠትና አቅም እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2050 በአፍሪካ የሕጻናት ቁጥር ከ900 ሚሊየን በላይ እንደሚሆን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ 40 በመቶ የዓለምን ክፍል የሚሸፍኑ ሕጻናትን ደህንነት መጠበቅ ግዴታ ነው ሲል አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ