ሕዳር 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአካባቢያቸው በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችና ባለሀብቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ የሚያስችል፤ አዲስ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ በሥራ ላይ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የመምህራን እና ትምህርት ቤቶች አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ንጋቱ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ ይህ አሰራር እያንዳንዱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመሳሳይ የትምህርት አሰጣጥ ዝግጅት እንዲኖረው ከማድረግ ይልቅ በአካባቢው በሚገኘው የተፈጥሮ ግብዓት ላይ መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራት ለፈጠራ ከፍተኛ ጥቅም እንዲያበረክት ያደርጋል።
ሥርዓቱ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ዋነኛ ልዩነት የሚመጡትን 'የፈጠራ ሥራዎች መመሳሰል' የሚያስቀር መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ "መምህራንና ተማሪዎች የተሻለ ውድድርና ጥራት ያለው የፈጠራ ሥራ እንዲያቀርቡ ያደርጋል" ብለዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) ሥርዓት መጀመሩ፤ የፈጠራ ሥራ ለሚሠሩ እና የምርምር ተግባር ለሚያካሂዱ ተማሪዎችና መምህራን የተሻለ ዕድል እንዲፈጥር ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ትምህርት ሥርዓቱ በማስገባት፤ የተሻለ ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎች ለማብቃት የተሻለ አሠራር መሆኑንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
አዲሱ አሠራር ተማሪዎች በአካባቢያቸው ያለውን እምቅ ሀብት ወደ ውጭ ማውጣት የሚያስችል ነውም ተብሏል።
አቶ ሙሉቀን አክለውም አሠራሩ በማንኛውም የትምህርት ዓይነት የሚማሩ፤ ጠንካራና ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለማፍራት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለዩ ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚወሰድ አማራጭ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሠራር ነው ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 'በአካባቢያቸው ሃብት' ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በሥራ ላይ ዋለ