ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ውስጥ ከአንድ ድርጅት ብቻ በቁጥር 425 የሚሆኑና ከ200 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ዶሮዎች ታርደውና ተበልተው ለሕብረተሰቡ ሊሸጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ለአሐዱ ሬድዮ አስታውቋል።

እንደሌሎች የምግብ ምርቶች ሁሉ በስጋና የስጋ ውጤቶች ላይ ከፖሊስ፣ ደንብ ማስከበር፣ ከንግድ ቢሮና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ቁጥጥር እንደሚደረግ የገለጹት፤ በባለስልጣን መስሪያቤቱ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ዳይሬክተር አቶ እጢፋኖስ ጌታቸው ናቸው።

Post image

እንደ በግ፣ ፍየልና በሬ የመሳሰሉ እንስሳት ገና ከምርመራ ሂደታቸው ጀምሮ ወደ ልኳንዳ ቤቶች ገብተው አገልግሎት ላይ ሲውሉ የተቀመጡበትን አግባብ እና ቦታው ለምግብ መሸጫነት የሚመጥን መሆኑን ጨምሮ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተናግረዋል።

የዶሮ ስጋን በሚመለከትም በቤት ውስጥ ግለሰቦች ከሚጠቀሙት ባሻገር ንፅህናው በተጠበቀ መልኩ አርደውና በልተው አሽገው የሚያቀርቡ ድርጅቶች መኖራቸውን ያነሱ ሲሆን፤ በተለያዩ ሱፐርማርኬቶች እና የምግብ መሸጫ ተቋማት እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም በግንዛቤ እጥረት በቁጥጥር ወቅት በተለያየ ምክንያት የሚሞቱ እንስሳትን አርደው መጠቀም እንደሚፈልጉ የሚገልፁ ሰዎች እንደሚያጋጥሟቸው ተናግረዋል።

ከዛም አልፎ ልኳንዳ ቤት ገብቶ የሚገኝበት አጋጣሚ መኖሩንም የገለጹ ሲሆን፤ "ልኳንዳ ቤት በቄራ ስለመታረዱና አስፈላጊውን መስፈርት ስለማሟላቱ ተረጋግጦ ሕገ-ወጥ ሆኖ ሲገኝ እንዲወገድ ይረጋል" ብለዋል።

ነገር ግን ተቋሙ የሞቱ እንስሳት በበሽታ ተይዘውም ሊሆን ስለሚችል ጤናማነቱ ያልተረጋገጠ ማንኛውንም እንስሳትን ሕብረተሰቡ አርዶ ለግሉም ይሁን ለገበያ ሽያጭ እንዳያቀርበው የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የትኛውም እንስሳት ላይ ቁጥጥር የሚደረገው ከእንስሳት ወደሰው የሚተላለፉ ከባድ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ታስቦ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም አግባብነት በሌለው ሁኔታ ዶሮዎችን የሚያርዱና የሚሸጡ መኖራቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ለማስተካከል በተሰራ ሥራም በ2018 ሩብ ዓመት ውስጥ ከአንድ ድርጅት ብቻ ምንጫቸው ያልታወቀ ከ200 ሺሕ ብር በላይ የሚያወጡ 425 ዶሮዎች ታርደውና ተበልተው ፍሪጅ ውስጥ በመገኘታቸው እንዲወገዱ መደረጉን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በሬና ፍየልም በተለያየ ቦታ ላይ ጤናማ ባልሆነ መንገድ አርደው ለሕዝቡ ሲሸጡ ተገኝተው እርምጃ መወሰዱን ያነሱ ሲሆን፤ ለአብነትም አንድ ድርጅት በግለሰብ ግቢ ውስጥ 3 በሬዎችን በምሽት አርዶ ሲያከፋፍል መያዙን ገልጸዋል።

ግለሰቡን ጨምሮ ግብረአበሮቹ በወንጀል ሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም አክለዋል።

በመሆኑም ተቋሙ ከሚያደርቀው ቁጥጥር ባሻገር ሕብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ድርጊት ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ ተቆጣጣሪ አካል በማሳወቅ የበለጠ ተባባሪነቱን ማጠናከር እንደሚገባው በመግለፅ፤ በ8864 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በትናንትናው ዕለት ባደረገው ድንገተኛ ኦፕሬሽን፤ በሾላ ገበያ የሞቱ ዶሮዎችን በማረድ እና በማሸግ ለተለያዩ ሱቆችና ሆቴሎች ለማከፋፈል ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦችን በመያዝ እርምጃ እንደተወሰደባቸው መግለጹ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ