ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አዳዲስ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ይዞ የመጣው ኦሜጋ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

በህብረት ሥራ ማህበር አዋጅ ቁጥር 985/09 በ2017 ዓ.ም በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመው ኦሜጋ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበር፤ በሴት የቦርድ አባላት የሚመራና በዘርፉ የረጅም ዓመት ልምድ ባካበቱ ባለሞያዎች የተቋቋመ መሆኑ ተነግሯል።

በዘርፉ የረጅም ዓመት ልምድ ባካበቱ ባለሞያዎች የተቋቋመው ማህበሩ፤ ላለፉት ወራት ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅቶችን ሊያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

በዘርፉ አሁን ላይ እየተተገበሩ ከሚገኙ የብድር አገልግሎቶች በተለየ መልኩ አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ መምጣቱን በመጠቆም፤ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ተመላክቷል።

Post image

በቡድን የሚመጡ ብድር ፈላጊዎች ልዩ የወለድ ቅናሽ እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ ሥራውን የሚጀምረው ኦሜጋ፤ ወላጆች ለታዳጊ ተማሪ ልጆቻቸው የት/ቤት ክፍያ ብድር እንዲያገኙ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጋር በተገናኘ የሚያስፈልጋቸውን ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቁሟል።

ለጤና አገልግሎት የሚውል ብሎም ለተለያዩ የውጭ ጉዞዎች የሚሆን ብድር ማህበሩ በልዩነት ይዟቸው ከመጡ ብድሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ብድር ፈላጊዎች የአጭር ጊዜ አነስተኛ ወለድ ያለው ብድር የሚያገኙ ሲሆን፤ ከወለድ ነፃ ብድር በማመቻቸት የተቀላጠፈ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁም ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚዲያ እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከሚሰሯቸው ሥራዎች ጋር በተገናኘ የፋይናንስ ችግር ለሥራቸው እንቅፋት እንዳይሆን ልዩ የብድር አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ማህበሩ ይፋ አድርጓል።

Post image

ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት የኪነ-ጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች ከኦሜጋ ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር ጋር በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ