ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ስር የሰደደ ኩላሊት በሽታ አስቀድሞ ለመከላከልና ሕክምና ለመስጠት የሚያግዝ መመሪያን ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚተገበረው ይህ መመሪያ፤ በጤና ጣቢያዎች እና መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ስር ለሰደደ ኩላሊት በሽታ አጋላጭ የሆኑ ግፊት እና ስኳር በሽታዎችን ምርመራ በማድረግ መለየት እና ሕክምና መስጠት የሚችሉበትን ሥርዓትን ማካተቱ ተነግሯል፡፡

ጤና ሚኒስቴር መመሪውን ይፋ ያደረገው ከፖፕሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል እና አስትራዜኔካ ከተሰኙ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት በተከናወነ መርሃ ግብር ላይም በይፋ መጀመሩ ተነግሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ በኢትዮጵያ ስር የሰደደ ኩላሊት ታማሚዎች ቁጥር ከ6 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ለበሽታው መስፋፋት ዋነኛ መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከልም የደም ግፊትና ስኳር በሽታ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ህይወት መለሰ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዜጎች የኩላሊት በሽታ እንዳያጋጥማቸው አስቀድሞ ለመከላከልና በበሽታው ዜጎች ከተያዙ በኋላም የሕክምና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ይፋ ሆኗል ብለዋል።
"ተላላፊ በሽታዎች ካልሆኑት መካከል አንዱ የኩላሊት በሽታ ነው" ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ለዚህ በሽታ ዋናኛ መንሰኤ የሆነው ደግሞ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ፣ አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለመስራትና በቂ ውሃ አለመጣት ዋና ጉዳይ ናቸው።
ችግሩን ለመቅርፍ መንግሥት፤ በዘርፉ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የጤና ተቋማትን አገልግሎት በመስፋት ትኩረት ሰቶ እየሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

የአስትራዜኔካ የጤናማ ልብ አፍሪካ ፕሮግራም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የደም ግፊት እና የልብና የደም ዝውውር በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የዚህ ፕሮግራም አካል ሆናለች።
ይህ አሁን ይፋ የተደረገው ስር ለሰደደ ኩላሊት በሽታ መመሪያ፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያመጡትና ጫና ለመቋቋም ያለመ ነው።
መመሪያው የጤና ስርዓቱን የመከላከል አቅም ለማጠናከር፣ ለጤና ባለሙያዎች ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ምርመራ እና አያያዝ ዙሪያ ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም፤ በሽታዎችን ቀደም ብሎ ለመለየት የሚያስችሉ መሣሪያዎችንና መመሪያዎችን ለማቅረብ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 850 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ስር በሰደደ የኩላሊት በሽታ የሚጠቁ ሲሆን፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የበሽታው ስርጭት 13 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱ ይገመታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ