ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል ከ10 ሺሕ ዓመት በላይ ተዳፍኖ የኖረው 'ሃይሊ ጉቢ' እሳተ ገሞራ ባለፈው እሁድ ፈንድቶ ፍንዳታው የለቀቀው አመድ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ላይ በመጓዝ ከባቢ አየር ውስጥ መለቀቁም የሚታወስ ነው።

ይህን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ቀጣይነትና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያጠና የተመራማሪዎች ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ-ፊዚክስ ፣ ህዋ-ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የፌስሞሎጂ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

Post image

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎቹ የየራሳቸው ሥም እንዳላቸው የተናገሩት ተመራማሪው፤ ብዙ ጊዜ 'ሆሎሲን ቮልካኖስ' እንደሚባሉ ጠቁመዋል፡፡

እነዚህም ባለፉት 10 ሺሕ ዓመታት ውስጥ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያካሄደ ከሆነ 'አክቲቭ' የሚባል ስያሜ እንደሚሰጠው አንስተዋል።

ከሰሞኑን የተከሰተው 'ሃይሊ ጉቢ' ግን እስካሁን ምንም አይነት የተመዘገበ ፍንዳታ ወይም እንቅስቃሴ ያላሳየ ቮልካኖ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ከአሁን ቀደም ከሚከሰቱ የእሳት ገሞራ ፍንዳታዎች አስቀድሞ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት እንደሚመዘገብ አንስተዋል። ከሃይሊ ጉቢ እሳት ገሞራ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ግን ብዙ የተመዘገበ ነገር እንደሌለ ተመራማሪው ገልጸዋል።

በሳተላይት እና በሌሎች የዘርፉ መሳሪያዎች የተሰበሰቡ መረጃዎ እንደሚያመላክቱት፤ በመሬት ንዝረት ደረጃ ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳልተመዘገበ ተናግረዋል።

በዚህ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ 'ሰልፈርዳይ ኦክሳይድን' ጨምሮ በብዙ ኪሎ ቶን የሚገመት የእሳተ ገሞራ አመድ ወደ ሰማይ የተረጨበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች ወደ አካባቢው መጓዛቸውን ተናግረዋል።

Post image

በቀጣይ በተመራማሪዎች የመስክ ምልከታ የሚገኙ ውጤቶች ይፋ እንደሚደረጉ የተናገሩት ተመራማሪው፤ ጉዳዩ ክትትል የሚፈልግ ነው ብለዋል ።

የፍንዳታው ጭስ እና አመድ በንፋስ ቀይ ባህርን በማቋረጥ በየመን አድርጎ ብዙ ርቀት የተጓዘ ቢሆንም፤ ለጤና አዋኪ የሆነው ነገር አብሮ ይጓዛል ማለት አይደለም ብለዋል።

ነገር ግን እሳተ ገሞራው እሳት የሚተፋ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው ቅርብ ርቀት ያሉ ማናቸውም ነገሮች ላይ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። ተመራማሪው አክ

Post image

ለውም፤ አደጋውን መከላከል ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ አደጋዎች ለምን ይፈጠራሉ? እንዴትስ መመዝገብ እና መከታተል ይቻላል? የሚለውን ለማጥናት፤ በሰው ኃይልና በመሳሪዎች የዘርፉን ተቋማት ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ይህን መሰሉ ክስተቱ በሚያጋጥምበት ጊዜ ሎጀስቲክስ ጨምሮ እገዛ በማድረግ ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ