ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሀሰተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን ይዘው ሲቀሳቀሱ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በርዋ ከበደ፣ ሙላት አባይ፣ ሳሙኤል ሙሉጌታ እና ጃኮ ፔንዞ የተባሉ ሲሆን፤ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ልዩ ሆቴል አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።

Post image

ሙላት አባይ የተባለው ተጠርጣሪ የተበደረውን ገንዘብ 'ልመልስልህ' በማለት ሀሰተኛ መቶ ዶላር ለጓደኛው እንደሰጠው የገለጸው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፤ ግለሰቡም ከጓደኛው የተቀበለውን ዶላር ወደ ባንክ በመሄድ ለመመዘር ሲሞክር ሀሰተኛ መሆኑ ስለተረጋገጠ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠቱን አስታውቋል።

ፖሊስም ጥቆማውን መነሻ በማድረግ በወንጀሉ አንደኛውን ተጠርጣሪ ከነአባሪው በመያዝ በተደረገ የአካል ፍተሻም 1000 ሀሰተኛ ዩሮ ሊገኝበትም ችሏል።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የማስፋት ተግባር ሳሙኤል ሙሉጌታ የተባለው ተጠርጣሪ እንደሰጣቸው ለፖሊስ መረጃ በመስጠታቸው፤ የተጠቀሰው ግለሰብ በቁጥጥር ስር በሚውልበት ጊዜም 1400 ሀሰተኛ ዶላር እንደተገኘበትም የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።

Post image

ፖሊስ ምርመራው የማስፋት ሥራውን በመቀጠልም ሦስተኛ ተጠርጣሪ ሀሰተኛ ዶላሩን ከየት እንዳመጣው ሲጠየቅ የውጭ ሀገር ዜጋ ወደሆነውና የውጭ ሀገር ዜግነት ወዳለው አራተኛ ተጠርጣሪ ጃኮ ፔንዞ መምራቱ ተገልጿል

አራተኛው ተጠርጣሪም 5 ሺሕ 600 ሀሰተኛ ዶላር መገናኛ አካባቢ ይዞ ሲቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር የዋለና በአጠቃላይ ከ8 ሺሕ በላይ የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ሕብረተሰቡ ሐሰተኛ የውጭ ሀገርም ሆነ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ኖቶችን ስርጭት ለመከላከል ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን መከላከል ይኖርበታል ሲልም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ