‎ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጃፓን መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የትግራይ ክልል ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎትን መልሶ ለመገንባትና ለማጠናከር ያለመ የሦስት የሕመምተኛ ማመላለሻ ተሸከርካሪ አምቡላንሶችና የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የተደረገው በኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ቢሮ በኩል ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም በጦርነቱ ምክንያት የተጓደለውን የድንገተኛና የሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን አቅርቦት ማሳደግ ነው ተብሏል።

Post image

አምቡላንሶቹ የተሰጡት በአዲዳዕሮ፣ እዳጋ አርቢ እና ፍረወይኒ ለሚገኙ ሦስት ሆስፒታሎች ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ሆስፒታሎቹ በተለይም የወሊድና የድንገተኛ ጊዜ ክፍሎቻቸው ሥራቸውን ያለማቋረጥ እንዲሰሩ የሚያስችሉ የሕክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶችም በድጋፍ መልክ ተበርክተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አማኑዔል ኃይሌ (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የአምቡላንሶቹ ድጋፍ አስፈላጊነት በትግራይ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ የጤና አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመለስና ለመደገፍ የታለመ ነው።

ኃላፊው አክለውም፤ አምቡላንሶቹ በድንገተኛ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠትም ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

Post image

በተጨማሪም፣ በክልሉ የሚገኙ የሕክምና ተቋማትን መልሶ በመገንባት፣ የውኃና የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን በማሻሻል እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ሪፈራልን በማጠናከር ላይ ድጋፉ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዶክተር አማኑኤል በክልሉ በኩፍኝና ወባ ወረርሽኝ ላይ ስርጭቱን ለመቀነስ የተቀናጁ ጥረቶች ጥሩ አፈጻጸም እያሳዩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጃፓንና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በትግራይ የጤና አገልግሎትን ወደነበረበት የመመለስና የአደጋ ጊዜ ምላሽ የመስጠት ሥራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል።

ይህ ድጋፍም የጃፓን ሕዝብና መንግሥት ከበጀቱ (JSB) በማሸጋሸግ በኢትዮጵያ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የተደረገ ነው።

ድጋፉን በቀጥታ ከኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ የተቀበሉት የኢፌድሪ ጤና ሚኒስትር ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) ሲሆኑ፤ በመድረኩም ለትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አማኑኤል ኃይሌ (ዶ/ር) አስረክበዋል።

Post image

በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ የውኃና የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ የሚስዮን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኔስቶ ሹንታሮ ለክልሉ የተደረገው ድጋፍ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማቅረብ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

ጃፓን ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ላሉ ከ150 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብና ኢንፌክሽንን ለመከላከል የተለያዩ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።

በመጨረሻም ጃፓን በኢትዮጵያ በተለያዩ የጤና ዘርፎች የሚደረጉ ድጋፎች ውጤታማ እንዲሆኑ፤ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቃለች።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ