‎ጥቅምት 6/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና በሌሎች የብዙኃን መገናኛዎች ላይ በሚተላለፉ የኪነ-ጥበብ ውጤቶች፤ አንድ ሙያ ወይም ሙያተኛን በሚያሳንስ መንገድ የሚቀለዱ ወይም የሚያፌዙ ጥፋተኞችን ለመቅጣት የሚያገለግል የሕግ አንቀጽ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ አለመካተቱን የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

ዓላማቸው 'ማዝናናት' እንደሆነ በሚናገሩና በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ በሌሎች ሚዲያዎች አማካኝነት በሚተላለፉ ድራማዎች እና የመዝናኛ ፕሮግራሞች፤ አንድን ሙያ ወይም ሙያተኛውን ለሳቅ መፍጠሪያ በግብዓትነት መጠቀም እየተለመደ መምጣቱ ይታወቃል።

አሐዱም "ይህንን መሰል ጥፋት የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል ወይ?" ሲል የሕግ ባለሙያዎችን ጠይቋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደስአለኝ "ይህንን መሰል ጥፋቶችን መከላከል የሚጠበቅባቸው የሙያ ማኅበራት ናቸው" ያሉ ሲሆን፤ በአንድ ሙያ ላይ መቀለድን ወይም ማፍንን ብቻ መሠረት በማድረግ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አንቀጽ ግን የለም ብለዋል፡፡

ይህን መሰል ጥፋትን ለመጠየቅ የሚያስችል አንቀጽ በወንጀል መቅጫ ሕጉ ላይ አለመኖሩ ፤ ችግሩን ለመቀረፍ አስቻይ ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"ተመልካችን ለማዝናናት እና ገበያ ተኮር የሆኑ ሥራዎች በሙያተኛው ላይ የሚያሳድሩት ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የጎላ መሆኑንና በሕግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ የወጣ መመሪያ አለመኖሩ ችግሩ ጠያቂም ተጠያቂም የሌለው እንደልብ የሚፈነጭበት መድረክ አድርጎታል" ብለዋል፡፡

ለችግሩ ሥር መስደድ በሙያተኞች፣ በሙያ ማኅበራት፣ በሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እርምጃዎች አለመውሰዳቸው፣ ጠንካራ የሕግ ማህቀፍ አለመኖር እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል ሲሉም አብራርተዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የሕግ ባለሙያ አበባው አበበ በበኩላቸው፤ ሙያን እና ሙያተኞችን የሚያሳንሱ ተግባራት ሊታረሙ እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በዋናነት የሙያ ማህበራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በሚተላለፉ ፕሮግራሞች አማካኝነት አንድን ሙያ እና ሙያተኛን ሥም የማጥፋት ተግባር የሚፈፀም ከሆነም፤ እርምጃዎችን መውሰድ አግባብ መሆኑንም የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል።

"መሰል ተግባራት ዜጎች በተለይም ተተኪው ትውልድ ለሙያ እና ሙያተኛው ያለውን ክብር እና አመኔታ እንዲቀንስ ከማድረጉም ባሻገር፤ ሙያተኞች ላይም ሥነ-ልቦናዊ ጫና ያሳድራል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ይህንን መሰል ድርጊቶች በመስፋፋታቸው ሙያዊ ክብር እንዳይኖር ማድረጉን በመግለጽ፤ "ይህ ለሙያተኞች ተጨማሪ ማነቆ እየሆነ ከመምጣቱ በተጨማሪ፤ ተግባሩ የሚከበር የሚወደድ ሙያ ያሳጣል" ሲሉ ስጋታቸውን አንስተዋል፡፡

የሕግ ባለሙያዎቹ ሙያን እና ሙያተኛን ለማስከበር የሚያገለግል የሕግ ማዕቀፍ የመኖሩን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በተጨማሪም 'በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ክስ ለማቅረብ የግል ተበዳይ መኖር አለበት' የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ ከሳሽ ተበዳይ ባልቀረበበት ተጠያቂ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል ብለዋል፡፡

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ