መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአውሮፓ ሕብረት ከጣሊያንና ስፔን መንግሥታት ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ያበረከተው 146 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የሕክምና መሳሪያ ድጋፍ የጤናው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ የሕክምና መሳሪያ እጥረት ይፈታል ሲል ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ከጣሊያንና ስፔን መንግሥታት ጋር በመተባበር፤ 146 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና መሳሪያዎችን ለስድስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።
በርክክብ ፕሮግራሙ ተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህርላ አብዱላሂ ባደረጉት ንግግር፤ የጣሊያን እና ስፔን ኮርፖሬሽን እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ላይ በትብብር እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሁን የተደረገው ድጋፍም በስድስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የስፔሻሊቲ ሕክምና ትምህርት እና የሕክምና ስርዓቱን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸው፤ በተለይ የጤናው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ የሕክምና መሳሪያ እጥረትን ይፈታል ብለዋል።
ድጋፉ የተደረገው ለጎንደር፣ ለመቀሌ፣ ለባህርዳር፣ ለሀረማያ፣ ለጅማ እና ለአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች መሆኑንም ገልጸዋል።

እነዚህም በዛሬው ዕለት ለዩኒቨርስቲዎቹ የተበረከቱት የሕክምና መሳሪያዎች ለሕጻናት ሕክምና ክፍል፣ ለማህጸንና ጽንስ ክፍል፣ ለአጥንት ሕክምና፣ ለድንገተኛ ሕክምና፣ እንዲሁም ሰመመን ሕክምና የሚጠቅሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ድጋፉ አልጋዎችን ጨምሮ ለእነዚህ ክፍሎች የሚሆኑ የተለያዩ የሕክምና መሳሪያዎች መሆናቸውን ሚኒስትር ዲኤታዋ አብራርተዋል።
ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ እና የጣሊያን መንግሥት በሽሬ እና በጎንደር ሆስፒታሎች የጤና አጠባበቅ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችል የ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ