መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የተቋሙ የዓመቱ ዋነኛ ዕቅድ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ምክር ቤት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
የምክር ቤቱ ዳይሬክተር አቶ መስኡድ ገበየሁባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች ሲቪል ማኅበራት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ ምክር ቤቱ የተቋቋመው በፍትሕ ሚኒስትር ሥር ያለው የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበር ግፊት ያደርጋል ብለዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ሲቪል ማኅበራት የማይናቅ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የግጭት ተሳታፊዎችን የሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት ለማምጣት መስራት የተቋማቸው የ2018 ዕቅድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቀደም ባሉ ዓመታት በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነትና አሁንም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለውን እገታና ግድያን ጨምሮ፤ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሽግግር ፍትሕ መቋቋማቸውን ጠቅሰዋል።
ለሰላም እጦት መነሻ የሆኑ ጉዳዮች ከመሠረቱ መፍትሔ እንዲያገኙ እንደ ሲቪል ማኅበራት ስለ ሰላም የተለያዩ ጥናቶች በማካሄድ፤ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የዓመቱ የምክር ቤቱ ትኩረት፣ በግጭት ሰበብ ለሚደርሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ የሀገርን ሰላምና ልማት ማረጋገጥ ላይ ነው ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ
