መስከረም 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ወጋገን ባንክ ደንበኞች በስዊፍት የሚላክን ዓለም አቀፍ ክፍያ የባንኩን ሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም በኦንላይን መከታተል የሚያስችላቸውን አገልግሎት ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱ በተለይም በገቢ እና ወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ኮርፖሬት ደንበኞች በስዊፍት ክፍያ ሲፈፅሙ፤ የክፍያ ትዕዛዝ በባንኩ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ገንዘቡ ለታለመበት ግለሰብ ወይም ተቋም እስከሚደርስ ድረስ ያለውን ሂደት ለመከታተል ያስችላቸዋል ብሏል።
በዚህም ከስዊፍት ጋር በተሳሰረው የባንኩ የክፍያ ስርዓት አማካይነት በሚደርሳቸው ልዩ የመከታተያ ቁጥር በመጠቀም በወጋገን ሞባይል መተግበሪያ በኩል በቀጥታ መከታተል እና ክፍያው መፈጸሙን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ወጋገን ባንክ ያስጀመረው የስዊፍት ክፍያ መከታተያ ስርዓት ባንኩ ለደንበኞቹ ሲሰጥ የቆየውን ዓለም አቀፍ የክፍያ አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈጣን፣ ግልፅነት የሰፈነበት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የበለጠ አስተማማኝ እንደሚያደርገው ገልጿል፡፡
እንዲሁም ደንበኞች ክፍያቸውን ወደ ባንኩ መምጣት ሳይጠበቅባቸው በስልካቸው መከታተል የሚያስችል መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡
በተያያዘም አዲሱ የኦንላይን ክፍያ መከታተያ ስርዓት ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን በፍጥነት እና በአስተማማኝ መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዲደርሱ በማስቻል፤ የሀገሪቱን ገቢ እና ወጪ ንግድ ለማቀላጠፍ እንዲሁም አዋጪ እንዲሆን በማገዝ በኩል የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡
ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት የወጋገን ሞባይል መተግበሪያ ሥር ስዊፍት የሚለውን አማራጭ በመከተል እና ልዩ የኦንላይን ክፍያ መከታተያ ኮድ ቁጥራቸውን (UTER) በማስገባት፤ መጠቀም እንደሚችሉ ባንኩ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ወጋገን ባንክ በስዊፍት የተላከን ዓለም አቀፍ ክፍያ በሞባይል መተግበሪያ መከታተል የሚያስች አገልግሎት አስጀመረ
