ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ደረቅ እንጀራን በየሰፈሩ በሚገኙ የሸቀጣ-ሸቀጥ ሱቆች ውስጥ ለጤና ጎጂ ከሆኑ ምርቶች እና ንጥረ-ነገሮች ጋር ለገበያ ማቅረብን የሚከለክል አዲስ መመሪያ በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚያውል የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል።

ይህ ውሳኔ የደረቅ እንጀራን ንጽሕና እና የሸማቹን ጤና ለመጠበቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በተቋሙ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው የመመሪያውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ለአሐዱ ሬድዮ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሸቀጣ-ሸቀጥ መደብሮች ውስጥ እንደ ሳሙና እና ኦሞ ያሉ የጽዳት እቃዎች፤ እንደ ፊሊት፣ በረኪና እና የአይጥ መርዝ ያሉ አደገኛ ኬሚካሎችን ጨምሮ ሌሎችም ከምግብ ጋር መቅረብ የማይገባቸው ምርቶች ለሽያጭ ስለሚቀርቡ ደረቅ እንጀራን ከእነዚህ አደገኛ ይዘት ካላቸው ጎጂ ንጥረ-ነገሮች ማራቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

Post image

አዲሱ መመሪያ ደረቅ እንጀራ ለገበያ እንዲቀርብ የሚፈቅድባቸው ቦታዎች፤ ለእንጀራ ብቻ ተብለው የተዘጋጁ የእንጀራ መሸጫ መደብሮች፣ ዳቦ ቤቶች እንዲሁም አጠቃላይ ምግብ አቅራቢዎች ማለትም ካፌ፣ ሬስቶራንት እና ሆቴሎችን ጨምሮ በምግብ ነክ ምርት አቅራቢ መደብሮች ውስጥ ብቻ ነው ተብሏል።

ዳይሬክተሩ አቶ እስጢፋኖስ፤ እንጀራ ከተመረተ (ከተጋገረ) በኋላ የሚጓጓዝበት መንገድም ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ነገሮች መካከል አንዱ እንደሆነ አብራርተዋል።

ደረቅ እንጀራ ከተመረተበት ቦታ ለተገልጋዩ በሽያጭ ወደሚቀርብበት ቦታ ሲጓጓዝ ትክክለኛ እና ለብክለት ያልተጋለጠ እንዲሆን መመሪያው ያስገድዳል።

የዝግጅት ሥራው የሚጠናቀቅበት እና ሥራ ላይ የሚውልበት ጊዜ ያልተጠቀሰው አዲሱ መመሪያ፤ "አሁን ያለውን 'ጎጂ መስሎ የማይታይ' የተሳሳተ አሰራር መቀየርን ዓላማው ያደረገ ነው" ተብሏል።

መመሪያው በተጨማሪም፤ እንጀራው የሚታሸግበት/የሚሸፈንበት ስስ ላስቲክ ለምግብ መጠቅለያነት የሚያገለግል መሆን አለመሆኑ ተጠንቶ; ደረጃ እንዲወጣለት የሚያስገድድ አንቀጽ እንደተካተተበትም አቶ እስጢፋኖስ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል።

Post image

ዳይሬክተሩ በመጨረሻም በርካታ ደረቅ እንጀራ አምራቾች በግል እና በቡድን በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ የእንጀራ ማምረት እና መሸጥ ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ጠቅሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘርፉ ቁጥጥር መጠናከሩ እንጀራን ከባዕድ ገነር ጋር ቀላቅሎ የማምረት ሕገ-ወጥ እና ኢ-ሞራላዊ አሰራር እንዲቀንስ ማድረጉን አስረድተዋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ