ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የዘመናት ያለፉ የፍትሕ፣ የመብትና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በሕዝባዊ ውይይት ይፈታል ተብሎ የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠው የአንድ ዓመት የሥራ ማራዘሚያ ጊዜ ሊጠናቀቅ የቀረው አጭር ወራት ብቻ ነው። ይህ ኮሚሽን ከተቋቋመ ሦስት ዓመት በኋላ ነው የሥራ ጊዜው የተራዘመለት።

ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሁኔታ በ11 ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ችሏል። ከዚህም በተጨማሪ የፌዴራል ደረጃና የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶችን አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ይሁን እንጂ፤ ኮሚሽኑ አሁንም ድረስ በዋናነት ሦስት ተግዳሮቶች ገጥመውታል። እነዚህም፤ በትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ አለመጀመሩ፣ የታጠቁ ኃይሎች እና የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ አለመሆናቸው ዋነኞቹ ናቸው።

ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት በትግራይ ክልል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ቢያደርግም፤ እስከ አሁን ድረስ ውጤት ሳያመጣለት እንደቀረ ኮሚሽኑ በይፋ ገልጿል።

Post image

በተመሳሳይ መልኩ፤ ኮሚሽኑ ከሥራው ራሳቸውን ካገለሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶችን ለማድረግ እና ወደ መድረኩ እንዲመለሱ ጥሪ ለማቅረብ ቢሞክርም፣ ፍሬ ማፍራት አልቻለም።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሰሞኑ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረገው ቆይታ፣ በዋናነት የፓርቲዎች ተሳትፎ እና ኮሚሽኑ ስለገጠሙት ተግዳሮቶች ተነጋግሯል። በዚህ ውይይት ላይ ሐሳባቸውን የገለጹት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ አካታች እና አሳታፊ ሆኖ እንዲሠራ በአዋጅ መደንገጉን ገልጸዋል።

Post image

ዋና ኮሚሽነሩ፤ "እንደ ሀገር ያለብንን ችግር ለመፍታት እና የተሻለች ሀገር ለመመሥረት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያደርገው ውይይት ወሳኝ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በዚህ ሂደትም 80 በመቶ የሚሆኑ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡ የተወሰኑት ግን አሁንም ራሳቸውን ከኮሚሽኑ ማግለላቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ተግዳሮት በተመለከተ ዋና ኮሚሽነሩ፤ ወደ ኮሚሽኑ ላለመምጣት የሚቀርቡት ችግሮች በአብዛኛው ፖለቲካዊ በመሆናቸው፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ከኮሚሽኑ ራሳቸውን ያገለሉ ፓርቲዎች በአብዛኛው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በእሥር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲሰጣቸው እና ሁሉንም አካታች ውይይት እንዲደረግ የሚሉ ናቸው።

ኮሚሽኑ ግን እነዚህ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ በመሆናቸው ምክንያት በኮሚሽኑ አቅም የሚፈቱ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ ለፌዴራል መንግሥት ያቀረበ ቢሆንም፣ በቂ ምላሽ እንዳላገኘም ተገልጿል።

ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ከኮሚሽኑ ራሳቸውን ካገለሉት ፓርቲዎች ወገን ጋር ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። እስካሁን ያለው ውይይት ፍሬ ያፈራ ባይሆንም ውይይቱን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ፓርቲዎቹ የሚያነሱት ጥያቄ ግን ኮሚሽኑን የሚመለከት አይደለም ብለዋል።

Post image

ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ጥያቄም ቢሆን፤ ከኮሚሽኑ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሮች ከመሰየማቸው አስቀድሞ በነበረው ሁኔታ የተመለከተውን ችግር መፍታት ኮሚሽነሮችን የሚመለከት አለመሆኑንም ጭምር ተናግረዋል። በተጨማሪም 'ግጭት መቆም አለበት' የሚል ጥያቄ መኖሩን ያነሱ ሲሆን፤ ግጭት እንዲቆም ሁሉም የሚፈልግ ቢሆንም እንዴት? በሚለው ላይ ግን መወያየት እንዳለብን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ የቀሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የትግራይ ክልል እንዲሁም የታጠቁ ኃይሎች አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶችን ማጠናቀቅ ይኖርበታል።

ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ለታጠቁ ኃይሎች ጥሪ ያደረገ ቢሆንም፤ ጥሪውን ተቀብለው በሂደቱ የተሳተፉ ታጣቂዎች የሉም። ይህ ኮሚሽኑ እንደ ተግዳሮት ከሚመለከታቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ሲሆን፤ ጥሪው ግን አሁንም ቀጥሏል።

Post image

ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) ግጭቶች ባሉበት ሁኔታ ላይ በመሆናችን ይህንን መፍትሔ ለመስጠት የፓርቲዎች አስተዋፅዖ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ከማግለል ይልቅ ተሳትፎ በማድረግ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በሰላም ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊነት አጠራጣሪ አለመሆኑን ያሉት ኮሚሽነሩ፤ "ተሳትፏችሁን ማሳደግ አለባችሁ" ሲሉም አሳስበዋል።

የሀገራዊ ምክክር መድረክ የፉክክር ሜዳ ሳይሆን ለሀገር አንድነት የምንተባበርበት መሆኑን ሁሉም ፓርቲ ሊገነዘበው እንደሚገባ አንስተዋል። "በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ አንዱ ፓርቲ አንዱን የሚጥልበት ሳይሆን፤ ተባብረን ነገ ዕድል ብናገኝ የምንመራትን ሀገር የማቅናት መሆን አለበት" ሲሉም ገልጸዋል።

Post image

ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ከዚህ በኋላ ያጠናቀራቸውን አጀንዳዎች ማጣራትና ዋናውን የሀገራዊ ጉባኤውን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይህ ሂደት እየቀጠለ፤ የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፣ የታጣቂዎች እና የታራሚዎች አጀንዳ ማሰባሰብ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን ላይ ከአራት ወራት ያነሰ ጊዜ ያለው ሲሆን፤ በየካቲት ወር ላይ የዋናውን ጉባኤ ለማካሄድ ማቀዱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በቀረው አጭር ወራት ውስጥ ሥራውን አጠናቆ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ኮሚሽኑ ከምርጫ በፊት ሥራውን እንደሚያጠናቅቅ እምነት እንዳላቸው ገልጸው ነበር። ካልተጠናቀቀ ግን ከምርጫ በኋላም ቢሆን ሥራውን መቀጠል እንደሚችል መናገራቸውም የሚታወስ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ