ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ነዋሪዎች እና ፖለቲከኞች የሚነሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ማከናወን እንዳልቻለ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ የክልሉን ነዋሪዎች አጀንዳ በአካል ተገኝቶ ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱ፤ "በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ዋናውን ጉባዔ ያዘገይብኛል" ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፤ "የምክክር ሂደቱ ሁሉን አካታች መሆን እንደሚገባው በአዋጁ ላይ በግልጽ በተደነገገው መሰረት የትኛውም አካል መሳተፉ ወሳኝ ቢሆንም፣ በሚነሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ምክንያት የትግራይ ክልልን ነዋሪ በምክክር ሂደቱ ማሳተፍ አዳጋች ሆኗል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ግብዓት የሚሆኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን በትግራይ ክልል ለመስራት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጀምሮ በመቀሌም ሆነ በአዲስ አበባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶችን በማካሄድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ኮሚሽነር መላኩ አስታውሰዋል።

Post image

አክለውም ኮሚሽኑ ያደረገው ጥረት በተለይ በክልሉ ካሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንዲያደርግ ቢያስችልም፣ በአብዛኛው የሚነሱት ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውና ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የሁሉንም ጥያቄዎች ምላሽ ከፌዴራል መንግሥት ብቻ የማግኘት አዝማሚያ እንዳለ ያነሱት ኮሚሽነሩ፤ ችግሮቹ ከሁለቱም ወገን ምላሽ ባለማግኘታቸው ኮሚሽኑ "ያቀደውን ሥራ በመወቅቱ መከወን አልቻልኩም" ሲል ገልጿል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ያካሄደው ውይይት ውጤት አለማምጣቱን ኮሚሽነር መላኩ ለአሐዱ ሬዲዮ አረጋግጠዋል።

የተጨመረለትን የሥራ ጊዜ ሊያጠናቅቅ ከ4 ወራት ያነሰ ጊዜ የቀረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል በስተቀር በ11 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በፌዴራልና በዲያስፖራው ማኅበረሰብ በኩል ያላውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በተቃውሞ እና ድጋፍ ታጅቦ የተሰባሰበው አጀንዳ ለዋናው ጉባዔ የሚቀርበው የካቲት ወር ላይ ስለመሆኑ አስቀድሞ ይፋ የተደረገው የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ