ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ድርድርን በአጽንዖት የሚጥል እና ግልጽ ማስፈራሪያዎችን የያዘ ንግግር አጥብቆ እንደማይቀበል አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ይህ አካሄድ የግብፅ መንግሥት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል አለመቻሉን የሚያሳይ መገለጫ መሆኑን አስታውቋል።
"አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ተዘፍቀው፣ በናይል ወንዝ ውሃ ላይ የብቸኝነት ባለቤትነት እንዳላቸው ያስባሉ" ያለው መግለጫው፤ እነዚህ አካላት የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን እና “ታሪካዊ መብቶች” የሚባሉትን በመጥቀስ በወንዙ ውሃ ላይ ያላቸውን የሞኖፖል ፍላጎት ደጋግመው እንደሚናገሩ አመላክቷል።

"ይህ አመለካከት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተገዥ፣ ደካማ እና የተከፋፈሉ ሀገራት የካይሮን ፍላጎት እንዲፈጽሙ በማሰብ፣ ኢትዮጵያን ያነጣጠረ የፀጥታ መደፍረስ ዘመቻ ከሚያካሂዱበት “ጊዜ ያለፈበት የአሠራር መመሪያ” የመነጨ ነው" ሲልም አስታውቋል።
ይህ የተሳሳተ አካሄድ እና ጥረት የአመራር እና የማሰብ ውድቀት መገለጫ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህም ኢትዮጵያን በፍጹም የማያስደነግጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
"ኢትዮጵያ የአፍሪካዊነት (Pan-Africanism) መርህን ለረጅም ጊዜ ያቀነቀነች እና በመላው አህጉር ያሉ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሎችን የደገፈች ረጅም እና ኩሩ ታሪክ ያላት ሀገር ነች" ሲልም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
"በጥንታዊ ሥልጣኔዎች ታሪክ የተመሠረተች እና ጠንካራ የአፍሪካ አብሮነት ልምድ ያላት በመሆኗ፤ ካይሮ ለማስወገድ የምትቸገረውን የቅኝ ግዛት ቅሪት ለመቀበል ምንም ዓይነት ቦታ የላትም" በማለት አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ተነሥቶ የሚፈሰው አባይ ወንዝ ለናይል ተፋሰስ ውሃ 86 በመቶ ያህሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ያለው መግለጫው፤ ልክ እንደማንኛውም ተፋሰስ ሀገር ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በዚህ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት እንዳላት አስታውቋል፡፡

ይህም ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና እኩል አጠቃቀም በመሠረታዊ የዓለም አቀፍ ሕግ መርህ የሚመራ በመሆኑ፤ "ኢትዮጵያ በወሰኗ ውስጥ በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠቀም ከማንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ የለባትም" ብሏል፡፡
"ባለፉት ጊዜያት ግብፅ በድርድር ውስጥ የምትሳተፍ በማስመሰል፣ በግትርነቷ እና በብቸኝነት የ'ይገባኛል' ጥያቄዋ አማካኝነት እድገትንና መፍትሔዎችን ስታደናቅፍ ቆይታለች" ያለው ሚኒስቴሩ፤ አሁን ግን ትርጉም ያለው ድርድርን በመቃወም የማስመሰል ፖሊሲዋ ይፋ እና ቀጥተኛ ሆኗል ሲል አስታውቋል።
"ግብፅ ድርድርን በመተው እና ግጭት ለመፍጠር በግልጽ በማሰብ የጥላቻ ንግግሯን አጠናክራለች" ያለም ሲሆን፤ ይህ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በሁሉም ተዋናዮች መወገዝ እንዳለበት ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
"እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የኢትዮጵያ የልማት ምኞቶችና ፕሮጀክቶች የአፍሪካ የራስ መተማመን እና እድገት መገለጫዎች ናቸው። ካይሮ አሁን በያዘችው አቋም እና ንግግር ከመጠመድ ይልቅ፣ የኢትዮጵያን ልማት ተቀብሎ እና ለጋራ ብልጽግናና ልማት የሚጠቅም የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር በቅን ልቦና መሥራት ብልህነት ነው" ብሏል።
ስለሆነም ዓለም እና አፍሪካ የሚያስፈልጋቸው ግጭትና ግብግብ ሳይሆን፣ የበለጠ ትብብርና ውይይት ነው ሲልም ገልጿል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ አሁን ያሉ እና መጪው ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የመጠቀም መብቷን አጥብቃ እንደምትጠብቅ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ በፍትሐዊነትና እኩልነት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ ለሁሉ ተጠቃሚነት መፍትሔዎች ክፍት መሆኗን አረጋግጧ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ