ሕዳር 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገሪቱ ከ40 በላይ የምግብ ዘይት አምራቾች እንደሚገኙና ከሀገር ውስጥ አምራቾች እየተገኘ ያለው የምርት መጠን 20 በመቶ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብ ዘይት ማህበር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

በየዓመቱ ከ42 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ዘይት በሀገር ውስጥ አምራቾች አማካኝነት እንደሚመረት ለአሐዱ የተናገሩት፤ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ትልቅሰው ለታ ናቸው።

የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ በሙሉ በአምራቾች ለመሸፍን ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ከግብዓት እህል አቅርቦት ጋር በተገናኘ መሻሻል መታየቱ የተቋማቱን የዘይት ምርት መጠን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን የተከሰተው የምግብ ዘይት እጥረት በሀገር ውስጥ አምራቾች የአቅርቦት ችግር ሳይሆን፤ ከውጭ ምርቶችን በሚያስገቡ ነጋዴዎች አማካኝነት መፈጠሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የዋጋ ጭማሪ እና መሰል ችግሮች ከሀገር ውስጥ አምራቾች ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም ጠቅሰዋል።

መሰል የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት ችግርን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ኹነኛ መፍትሔ እንደሆነ ተናግረዋል። የሀገር ውስጥ የዘይት ምርቶች የጥራት መጠንም ቢሆን ከፍተኛ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርታቸውን እንዲያሳድጉ መንግሥት በተለያዩ መስኮች መደገፍ እንዳለበት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አሳስበዋል፡፡

ከምግብ ዘይት ጋር በተገናኘ ዜጎች የመሸጫ ዋጋ መናርና የአቅርቦት እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው ሲያነሱ ይደመጣል።

ለሚስተዋሉ ችግሮች በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ በዋናነት የግብዓት እጥረትና የአምራቾች ከገበያ መውጣት ዋነኛ ተጠቃሾች መሆናቸው ይገለጻል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ