ሕዳር 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጤና መድህን አገልግሎትን በብድር ማደስ የሚቻልበትን የአሰራር ስርዓት እያመቻቸ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍሎች በአብዛኛው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በብድር ማደስ የሚቻልበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን፤ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም አርሶ እና አርብቶ አደሮች የጤና መድህን ተጠቃሚዎች በመሆናቸው የማደሻ ጊዜው ከጥቅምት እስከ ታሔሳስ ባሉት ምርት በሚሰበሰብባቸው ወራት እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት በአንዳንድ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሰብል ሊጎዳ ስለሚችል የጤና መድህን አገልግሎትን ለማሳደስ ገንዘብ ላይገኝ ይችላል ብለዋል፡፡
ይህንን ጫና ለመቀነስና አስተማማኝ የሆነ የቴና መድህን እድሳት ስርዓትን ለመዘርጋት እንዲያስችል ከባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር የብድር አገልግሎቶች እየተመቻቹ ነው ብለዋል፡፡
በተያያዘም የመረጃ ብክነትን ለመቀነስ እና ሆስፒታሎች እና ሌሎችም የጤና ተቋማት ለወረቀት የሚያወጡትን ወጪ ለመቀነስ የአሰራርና የክፍያ ስርዓትን ጨምሮ ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም 40 የሚሆኑ ሆስፒታሎችን የአሰራርና የክፍያ ስርዓት ከወረቀት ነጻ ማድረግ ተችሏል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ ትላልቅ ሆስፒታሎች በዓመት ለወረቀት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣሉ የተባለ ሲሆን፤ ከወረቀት ነጻ የተደረጉት ሆስፒታሎች ይህን ኪሳራ መቀነስ እንደቻሉ ነው ወ/ሮ ሳህረላ የገለጹት፡፡
የዲጂታል ስርዓቱን በማስፋት መድሃኒት ቤቶች ላይ የሚገኙ መድሃኒቶች እና ዋጋቸውንም ጨምሮ መለየት የሚያስችል አሰራር በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የጤና መድህን አገልግሎትን በብድር ማደስ የሚቻልበት አሰራር እየተዘረጋ ነው ተባለ