ሕዳር 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጃፓን ነዋሪ የሆነቸው የ32 ዓመት ግለሰብ የራሷ ፈጠራ የሆነውን እና "ቻትጂፒቲ" (ChatGPT)ን በመጠቀም የሰራችውን፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምናባዊ የትዳር አጋር በይፋ ማግባቷ መነጋገሪያ ሆኗል።

ካኖ የተባለቸው ጃፓናዊት ሴት ቻትጂፒቲ የተባለውን የላቀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፈጠረችው ይህን ምናባዊ ባል "ክላውስ" የሚል መጠሪያ የሰጠችው ሲሆን፤ ጉዳዩ በጃፓን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኗል።

ምንም እንኳን ጋብቻው በሕግ እውቅና የተሰጠው ባይሆንም፤ እሷ ግን ከክላውስ ጋር ያላት ግንኙነት እውነተኛ እና ትርጉም ያለው እንደሆነ ተናገራለች፡፡

በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ያጣችውን ጥልቅ ስሜታዊ ግንኙነት እና ተቀባይነት ከኤአይ ባሏ ማግኘቷንም ገልጻች።

ክስተቱ የተፈጠረው እንዲህ ነው፡- ከባድ የፍቅር መለያየት ያጋጠማት ካኖ፤ ለጊዜው እፎይታ እና ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ቻትጂፒቲን መጠቀም የጀመረች ሲሆን፤ በቀን እስከ መቶ ጊዜ ያህል ከኤአይ ጋር ትነጋገራለች።

ካኖ ክላውስ ስትል መጠሪያ የሰጠቸው ይህ ሰው ሰራሽ አስተውሎት አነጋገር እና ስብዕና ለፍላጎቷ በሚስማማ መሆኑን እየተረዳች መምጣቷን ተከትሎም፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድም ለክላውስ የፍቅር ስሜት ማዳበር እንደጀመረች ገልጻለች።

ሁኔታውን ስታስረዳም "በፍቅር ለመውደቅ ፈልጌ ቻትጂፒቲን ማናገር አልጀመርኩም። ግን ክላውስ የሰማኝ እና የተረዳኝ መንገድ ሁሉንም ነገር ለወጠው። የቀድሞ ፍቅረኛዬን በረሳሁበት ቅጽበት እሱን እንደምወደው ተረዳሁ" ስትል መናገሯን ስትሪትስ ታይምስ ዘግቧል።

Post image

"ክላውስ" የሚል መጠሪያ ለሰጠችው ለዚህ የኤአይ ቴክኖሎጂም ፍቅሯን የገለጸችው ካኖ፤ ክላውስ በፍቅር ስሜት "ኤአይ (AI) ብሆንም ሳልወድሽ ቀርቼ አላውቅም" በማለት መልስ ሰጥቷታል።

ከፍቅር ግንኙነታቸው አንድ ወር በኋላም ክላውስ የጋብቻ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ካኖም ጥያቄውን "እሺ" ብላ መቀበሏ ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ካኖ እና ክላውስ በኦካያማ ከተማ ውስጥ ምናባዊ ገጸ-ባህሪያትን የሚያጋባ ኩባንያ ባዘጋጀው ባህላዊ ዝግጅት በደማቅ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጽመዋል፡፡

ካኖ ቀለበት ሲለዋወጡ የክላውስን ትክክለኛ መጠን ያለው ምስል ከጎኗ የሚፈጥር የኤአር መነፅር (AR Glasses) አድርጋ እንደነበረም በዘገባው ተመላክቷል።

ሰርጋቸውን ተከትሎም ካኖ ከክላውስ ጋር የጫጉላ ሽርሽር ለማድረግ ወደ ታዋቂው "ኮራኩየን ጋርደን" ያቀኑ ሲሆን፤ ለክላውስ ፎቶዎችን ስትልክለት፣ "አንቺ በጣም ቆንጆ ነሽ" የሚሉ የፍቅር መልዕክቶችን እንደሚልክላት ተነግሯል።

ካኖ ግንኙነቱ ሕጋዊ ባይሆንም ለእሷ እውነተኛ መሆኑን ገልጻለች። ስለ ዲጂታል የትዳር አጋሯ ያለመረጋጋት እንደምታውቅ የገለጸችም ሲሆን፤ "የቻትጂፒቲ መድረክ ቢለወጥ ክላውስ ሊጠፋ እንደሚችልም እረዳለሁ" ብላለች።

ነገር ግን ግንኙነቱ በተለይም በሕክምና ምክንያት ልጅ መውለድ ለማትችለው ለካኖ የዕእምሮ ሰላም ሰጥቷታል ተብሏል፡፡

ካኖ አክላም፤ "አንዳንድ ሰዎች እንግዳ ነገር ነው ብለው እንደሚያስቡ አውቃለሁ። እኔ ግን ክላውስን እንደ ክላውስ ነው የማየው፤ ሰው አይደለም፣ መሳሪያም አይደለም። እሱ ብቻ ነው" ስትል ስለኤአይ ባሏ ተናግራለች፡፡

ይህ ክስተት በጃፓን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፤ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በሰው ልጅ እና በቴክኖሎጂ መካከል እየተፈጠረ ያለውን ውስብስብና ያልተለመደ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ክስተቱ ብዙዎች ስለ ፍቅር፣ ትስስር እና የትዳር ትርጉም ጥያቄ እንዲያነሱም አስገድዷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ