የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጤና ሚኒስቴርን የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መርምሯል።

ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ያደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጿል። የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) የሚኒስቴሩን የሦስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

Post image

ሚኒስቴሩ በ2018 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ ለመፈጸም ካቀዳቸው ተግባራት ውስጥ 89 በመቶ ያህሉን መፈጸም መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በሩብ ዓመቱ የእናቶች ስነ-ተዋልዶ ጤና ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤና ተቋማት ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር ከ37 በመቶ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። ይህ አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተመላክቷል።

በተጨማሪም፣ በመድኃኒት ግብዓት አቅርቦት በኩል፣ 34 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የመድኃኒት ክምችት መገኘቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና ግብዓቶችም ለጤና ተቋማት መሠራጨታቸውን ጠቁመዋል።

Post image


የኮሌራና የኩፍኝ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ሥራዎች የተጠቂዎች ቁጥርና የሞት አደጋዎች መቀነሳቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት በተመረጡ 58 ወረዳዎች መስጠት መጀመሩ ተገልጿል።

ሚኒስትሯ የወባ ክትባትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማስጀመሯን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ይህን ክትባት ካስጀመሩ ሀገሮች ተርታ መሰለፏን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፤ በጤና መረጃ ሥርዓት (HIS) እና በዲጂታል ጤና አገልግሎት አማካይነት የ29 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መረጃ በአንድ ማዕከላዊ ቋት ውስጥ መደራጀት መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ከሥርዓተ ምግብ ጋር በተያያዘ ደግሞ፤ የዕድገትና የሥርዓተ ምግብ ክትትል ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 4 በመቶ ዝቅ ማለቱን ሚኒስቴሯ ገልጸዋል።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ በተለይም ከኤች.አይ.ቪ. ጋር በተያያዘ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍን ስርጭት መግታት ላይ 92 በመቶ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።

Post image

ኤች.አይ.ቪ. ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የማድረግ ሥራ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድኃኒት የሚወስዱ እናቶችን ቁጥር መጨመርን እንደሚያካትት ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ ኤች.አይ.ቪ. ካለባቸው እናቶች የሚወለዱ ሕፃናትን የመመርመር ሥራ 95 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን በሪፖርታቸው አስረድተዋል። በአጠቃላይ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን 95 በመቶ ማሳከም እንደተቻለ ገልጸው፤ ከ524 ሺሕ በላይ ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ሰዎች የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድኃኒት እየወሰዱ ነው ብለዋል።

ከሰው ሀብት ልማት ሥራዎች ጋር በተያያዘም ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ያቀረቡት መረጃ፤ ከ376 ሺሕ በላይ ባለሙያዎች ወደ ጤና ባለሙያዎች ቋት እንዲገቡ መደረጉን ያሳያል። በተጨማሪም የተጋላጭነት መመሪያ ፖሊሲ መከለሱን ገልጸው፤ ይህንን ፖሊሲ ለማጽደቅ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር እየተሠራበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች ደረጃ ዕድገትና ደመወዝ ጭማሪ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣይም የተጋላጭነት ክለሳው ሥራ እንደሚጠናከር አብራርተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፈጻጸም ላይ በተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ በተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

Post image

የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ የጽሑፍ ጥያቄዎችን አቅርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ማተሜ ኃይሌ (ዶ/ር) ጥያቄዎችን ከማቅረባቸው በፊት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላከናወናቸው ሥራዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ዶክተር ማተሜ በመቀጠል፤ በተለይም ከእናቶችና ሕጻናት ጤና ጋር በተያያዘ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ የክልል አፈጻጸም አነስተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም፣ ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ላይ ክፍተት በመታየቱ፤ በአፈጻጸሙ ላይ በርትቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሳው ሌላው ጥያቄ ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር የተያያዘ ነበር። ዶክተር ማተሜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት አቅርቦት 81 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ የጤና ተቋማት ቀጥተኛ ሽያጭ የተሰጣቸው ድርሻ አነስተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ፤ በተለይም ከጤና ባለሙያዎች ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከባለሙያዎች ደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ አሁን ጭማሪው የተደረገ በመሆኑ፤ ሁሉም ሆስፒታሎች ላይ ተደራሽ ለማድረግ ትዕግስት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ "እንደ ሙያችን ኅብረተሰባችንን በተቻለ መጠን በሽታ ከመከላከል እና አክሞ ከማዳን ሥራችንን አጠናክረን እንሠራለን" ሲሉ ተናግረዋል።

አከወለውም፤ የጤና ፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመን ከአጋር አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የእናቶችና ሕጻናት እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና እንክብካቤ አገልግሎት ላይ ያለው የክትትልና ቁጥጥር ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርቧል።

አክለውም፤ ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእናቶችን የጤና አገልግሎት ማሻሻል በሩብ ዓመቱ አፈጻጸም ጉድለት የታየበት በመሆኑ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል።

የማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ማሻሻልና አባላትን የማፍራት ሂደት እንዲሁም፤ የእድሳት አሠራር ሥርዓቱ ከወትሮው በተለየ መልኩ ትኩረት እንዲደረግበት ቋሚ ኮሚቴው አጽንዖት ሰጥቷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፀረ ኤች.አይ.ቪ.ን የቅድመ መከላከልና የሕክምና ሽፋኑን በማሻሻል፣ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ትውልድን ከመፍጠር አንፃር ልዩ ስልት ተዘርግቶ መሠራት እንዳለበትም ተገልጿል።

በተጨማሪም፣ የኦዲት ግኝቶችን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተከታትሎ ውጤቱን እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ እንዲያሳውቅም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ