ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም. በትራኮማ ምክንያት ለዓይን ሞራ ግርዶሽና ለከፍተኛ የዕይታ ችግር ላጋጠማቸው ከ80 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ቀዶ ሕክምና መሰጠቱን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ህይወት ሰለሞን (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ቀዶ ሕክምናውን ያከናወኑት ከ80 ሺሕ በላይ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው አግኝተዋል።
በተለይ በእድሜ የገፉና በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቃው ትራኮማ የሚያስከትለውን የጤና ችግር ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር ሚኒስቴሩ በተያዘው ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና በዓለም አቀፍ ደረጃ በመነፅር ሊስተካከል በሚችል የዕይታ ችግር ምክንያት ከ64 በመቶ በላይ ሰዎች እየተሰቃዩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ማንደፍሮ ስንታየሁ (ዶ/ር) በዓለም ዙሪያ በቀላሉ ሕክምና የሚያገኙት ታማሚዎች 36 በመቶ ብቻ ናቸው" ብለዋል፡፡
ቀሪዎቹ 64 በመቶ ሰዎች በቀላል ሕክምና ሊስተካከል በሚችል እክል ምክንያት ለሕመም ስቃይ እና ለዓይነ-ስውርነት ይዳረጋሉ፡፡
የአቅርቦት ውስንነትና የመነፅር ዋጋ መወደድ ዋነኛ ችግሮች ናቸው የተባሉ ሲሆን፤ በተለይ ችግሩ ወደ ገጠራማው ክፍል በስፋት ይስተዋላል ያለው ማኅበሩ፤ ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላትና ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ህይወት ሰለሞን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ6 ቢሊዮን በላይ ለእይታ ችግር የተጋለጡ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 1 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ለችግር የተጋለጡ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የቅድመ ምርመራ በማድረግ እንዲሁም በቀላል ሕክምና ማለትም በመነፅር በሚስተካከሉት ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የዓይን ሞራ ግርዶሽ ለገጠማቸው ከ80 ሺሕ በላይ ሰዎች ቀዶ ሕክምና መከናወኑ ተገለጸ
64 በመቶ የዓለም ሕዝብ በቀላሉ በመነጽር ሊስተካከል በሚችል የዕይታ ችግር ይሰቃያል ተብሏል
