ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጥፋተኛን ለመቅጣት የተሸከርካሪ ታርጋ መፍታት እንደማይቻል አስታውቋል፡፡
"በተሸከርካሪዎች 'ጥፋት ሲፈጸም ታርጋ ይፈታ' የሚል ሕግ የለም" ያሉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጥፋት ሲፈጸም የተሸከርካሪ ሰሌዳ መፍታት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰሌዳ በመፍታት ጥፋተኛ ይቀጣል ማለት እንደማይቻል እና በተሸከርካሪዎች ላይ 'ተግባራዊ ይደረጋል' የተባለው አዲሱ ሰሌዳ እንደማይፈታ የገለጹ ሲሆን፤ ጥፋተኛን ለመቅጣት ሰሌዳ መፍታት አግባብነት የለውም ነው ያሉት፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ በርሆ ሃሰን የተሸከርካሪ ታርጋ እንዳይፈታ እየተሰራ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ እንዲተገበር ለማስቻል የተሸከርካሪዎች ታርጋ ሳይፈታ የቅጣት ክፍያ በበይነ መረብ እንዲፈጽም እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዲኤታው አክለውም ታርጋ መፈታት ያለባቸው የተለዩ ምክንያቶች እንዳሉ በመግለጽ፤ ለቅጣት አይነት ሁኔታቸዎች ግን የተሸከርካሪ ታርጋን መፍታት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በዘንደሮ ዓመት የተሸከርካሪ ታርጋ እንዳይፈታ ይሰራል ሲል ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በሀገሪቱ የሚገኙ ተሸከርካሪዎች በአዲሱ ሰሌዳ ሙሉ ለሙሉ እዲቀየር ይደረጋል ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ አዲሱን ሰሌዳ ከውጭ ተመርቶ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አክለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ አዲሱ የተሸከርካሪ ሰሌዳ እንዲመረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቀጣይ አዲሱ ታርጋ በሀገር ውስጥ እንዲመረት ለማስቻል መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በተያዘው በጀት ዓመት ለቅጣት በሚል የተሸከርካሪ ታርጋ እንዳይፈታ ይደረጋል ተባለ
