ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚደርሰውን ሃብታቸውን የእንስሳት መኖ ግዥ ላይ እንደሚያውሉ ግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በኢትዮጵያ ለእንስሳት መኖ ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መጥቷል።

በዚህም "እንደ ሀገር በእንስሳት እርባታ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፤ ትርፍ ሊያገኙ ቀርቶ ወጪያቸውን እንኳን ለመሸፈን ተቸግረዋል" የሚሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ ለዚህ ምክንያቱም አርሶ አደሮቹ ከፍተኛ ወጪ የእንስሳት መኖ ግዥ ላይ ስለሚያወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መኖ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከግብር ነፃ አለመሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው እና ይህም እንደ ወተት እንቁላልና ስጋ ያሉ ምርቶች ዋጋቸው እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

"የእንስሳት መኖ ላይ የሚጣለውን ግብር እንዲቀር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመንግሥት አቅርበናል" የሚሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ ነገር ግን ችግሩ እስካሁን ድረስ ሳይቀረፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

አክለውም "የእንስሳት መኖ መወደድና ከግብር ነፃ አለመሆኑ ሀገራዊ አጀንዳ ተደርጎ ተይዟል" ያሉ ሲሆን፤ እስከመጪው ጥቅምት መጨረሻ ድረስ ችግሩን ሊቀርፍ የሚችል ውጤት ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ