ሕዳር 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በአብሮነት እራት ተመግበው በጠና ከታመሙ ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላት ውስጥ፤ አባወራዉ ከስድስት ልጆቹ ጋር ሰባት የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸዉ ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ የወንጀል መረጃ ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ምክትል ኮማንደር ያለው ተመስገን፤ በወረዳው መሰረተ ወገራም ቀበሌ ዳሾ ቆቶ ተብሎ በሚጠራው መንደር ሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 1:00 ሰዓት ስምንቱ የቤተሰብ አባላት አብረዉ እራት ከተመገቡ በኋላ በድንገት መታመማቸውን ተናግረዋል።
በአብሮነት እራት እንደተመገቡ ብዙም ሳይቆዩ ከፍተኛ ለሆነ ሕመም መዳረጋቸውን መረጃ የደረሳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተጎጂዎችን ሕይወት ለማትረፍ ተረባርበው ወደ ሆስፒታል ማድረሳቸው ነው የተገለጸው።
ነገር ግን ከተጎዱ የቤተሰቡ አባላት የ5 ዓመቱ መንግሥቱ ኃይሌ፣ የ7 ዓመቱ መክብነ ኃይሌ እና የ17 ዓመቱ ተክሉ ኃይሌ የተባሉት ሦስቱ ወንድማማቾች በዕለቱ ሆስፒታል እንደደረሱ ሕይወታቸው ማለፉን ፖሊስ ተናግሯል።
የተቀሩ ተጎጂዎችን ሕይወት በሕክምና ለማትረፍ ሐኪሞች ያልተቋረጠ ጥረት ቢያደርጉም፤ የ14 ዓመቷ መቅደስ ኃይሌ እና የ15 ዓመቱ ገብሬ ኃይሌ የሁለቱ እህትና ወንድም ሕይወት በማግስቱ ሕዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 11:00 ሰዓት ሲያልፍ የሟቾች ቁጥር አምስት ደርሷል።
ከተቀሩት ተጎጂዎች ደግሞ የ1 ዓመት ከ7 ወሩ ሕጻን ሲሳይ ኃይሌ ሕዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጥዋት 2:00 ሰዓት ላይ ሕይወቱ ሲያልፍ፤ የስድስቱ ሟች ልጆች አባት የሆነው የ46 ዓመቱ አቶ ኃይሌ አበራ ሕዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለሊት በሰመመን ዉስጥ ሆኖ ከእንቅልፉ ሳይነቃ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል፡፡
የባለቤቷንና የስድስት ልጆችዋን ህልፈት ያልተረዳችው ወይዘሮ ዳመነች ደንበል፤ በሚኒሊክ ሆስፒታል በሕክምና እየተረዳች በሕይወት መኖሯንም የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ተጎጂዎች የተመገቡት ምግብ የተመረዘው በማንና እንዴት? የሚለዉን እውነታ በማጣራት ለማረጋገጥ፤ ከምስራቅ ጉራጌ ዞን እና ከመስቃን ወረዳ የተወጣጣ የምርመራ አጣሪ ግብረ ኃይል አዋቅሮ ምርመራ የማጣራቱን ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡
ኮማንደር ያለዉ ተመስገን የምርመራ ግብረ ኃይሉ 'በድርጊቱ የሌሎች እጅ ሊኖር ይችላል' በሚል ጥርጣሬ አስር ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዉሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
"ተጎጂዎች በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ሕክምና ተከታትለዋል" ያለው ፖሊስ፤ የሟቾች የአስክሬን ምርመራ ውጤት እየተጠበቀ መሆኑንና ስለጉዳዩ የተሻለ ፍንጭ ሊሰጥ እንደሚችል መረጃ ሊገኝ እንደሚችል መገመቱን አሐዱ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የተመረዘ ምግብ በልተው ከታመሙ 8 የአንድ ቤተሰብ አባላት ዉስጥ የ7ቱ ሕይወት ማለፉ ተገለጸ