ጥቅምት 10/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ስርጭቱ በድጋሚ መጨመር ማሳየቱን ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የቫይረሱን ሥርጭትን የመቆጣጠር እና በ2030 ደግሞ ዜሮ የማድረስ ግብ አስቀምጣ እየሰራች እንደምትገኝ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት ዳግም መጨመር ማሳየቱ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለስርጭቱ መጨመር ምክንያት ከሆኑት መካከል ለጉዳዩ ተሠጥቶት የነበረው ትኩረት መቀዛቀዝ ዋነኛው እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ኤች አይቪ/ኤድስ ዛሬም ቢሆን በማህበረሰቡ ዘንድ አሳሳቢ የጤና ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

ይሁን እንጂ የቫይረሱ ስርጭት ምጣኔ ከ2010 በፊት ከነበረው ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር የቀነሰ ቢሆንም፤ በ2030 ምጣኔውን ዜሮ ለማድረስ ከተቀመጠው ግብ አንፃር በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ከፍተኛ ስርጭት አሁንም በርካታ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ስርጭቱ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች አከባቢ እየጨመረ መምጣቱንም ሚንስትር ዲኤታው ጨምረው ጠቁመዋል።

ቫይረሱን ችላ በማለትና ጥንቃቄ ባለማድረግ ምክንያት፤ በማዕድን ማውጣትና በፋብሪካዎች ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች እንዲሁም በቀን ሠራተኞች ላይ የስርጭቱ ምጣኔ ከፍ ማለቱን መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም ስርጭቱን ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 8 ሺሕ 257 የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚያዙ እና 11 ሺሕ 322 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ምክንያት በየአመቱ እንደሚሞቱ በ2015 ዓ.ም የወጣው ሀገራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ግምት መረጃ ያሳያል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ