ጥቅምት 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ቤት ወይም ቪላ አልፋ እስከ ጥቅምት 2018 ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ቢባልም፤ ክፍት ከመደረጉ በፊት መሰራት ያለባቸው ሥራዎች ገና ባለመጠናቀቃቸው እስከ ሚያዚያ ወር ሊቆይ እንደሚችል ነው የተገልጿል፡፡

የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ካረፉ በኋላ ዝግ ሆኖ እስካሁን የዘለቀው ቪላ አልፋ፤ የተለያዩ የጥገና ሥራዎች እየተሰሩለት ነው ቢባልም ግን ለሕዝብ እይታ ተከልክሎ 14ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

Post image

ቪላ አልፋ የጥገና ሥራው ከመጀመሩ በፊት ውስጡ ያሉት ተንቀሳቃሽ የጥበብ ሥራዎች እና ሌሎችም ንብረቶች ወደ ቅርስ ባለ-ስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲሄዱ ተደርጎ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ከመሬት በታች በሚወጣ እና ከላይ በሚዘንብ ዝናብ ቪላ አልፋ በጣም ተጎድቶ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ከውጭ ሀገራትም ይሁን ከሀገር ውስጥ የአርቲስቱን ሥራዎች እየተመለከቱ ባለሙያዎች ትምህርት ለመውሰድ በሚችሉበት ደረጃ ጥገናው ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

እንደ ሙዚየም የሚደራጅ በመሆኑ ጊዜ እንደወሰደም ነው የተገለጸው፡፡

Post image

የእድሳቱ ሥራ ተጠናቆ የርክክብ እና ቅርሶችን በቦታቸው የመመለስ ሥራዎች ብቻ ቀርቷል ሲሉም የብሄራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም ግርማይ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"የእድሳቱ ሥራ ጥንቃቄዎችን የሚጠይቅ ነበር" ያሉት አቶ እንዷለም፤ የርክክብ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ቪላ አልፋን በ2018 እስከ ሚያዚያ ወር ለእይታ ክፍት ለማድረግ ታስቧል ነው ያሉት፡፡

የእድሳት ሥራው 65 ሚሊየን ብር እንዳስወጣ ከዚህ በፊት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የእድሳት ሥራው በምዕራፎች የተከፋፈለ ነበር ነው የተባለው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ