ጥቅምት 10/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)1 ሺሕ 500 ብር ይከፈል ለነበረው ጤና መድህን ከ7 ሺሕ እስከ 10 ሺሕ ብር እንድንከፍል እየተገደድን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሐዱ ያቀረቡ የአዲስ አባባ ጤና መድህን ተገልጋዮች ገልጸዋል፡፡

እየተጠየቅን ያለነው የጤና መድህን ክፍያ የከተማዋን ነዋሪ አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ አያደለም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ባለፈው ዓመት ለአገልግሎቱ ይከፈል የነበረው ክፍያ የዚህ ዓመት ክፍያ ግን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል። በዚህም የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ ባሻገርም ክፍያው በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩ የተነሳ የደሃ ደሃ ለሆኑት ማህበረሰብ ክፍሎች ለአገልግሎቱ 2 ሺሕ 200 ብር እየከፈሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሐዱ የነዋሪዎችን ቅሬታ ተቀብሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ኢብራሂም ተካን ጠይቋል፡፡

ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽም ባለፉት ጊዜያት ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ክፍያ ይከፍል እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት የተሻለ ገቢ ያለው ዜጋ የተሻለ ክፍያ እንዲከፍል እና አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው በአቅሙ እንዲከፍል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

Post image

በዚህ የክፍያ ሂደትም የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች 10 ሺሕ 500፣ ደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች 6 ሺሕ 900 እንደሚከፍሉ አንስተው፤ አብዛኛው ነዋሪ 2 ሺሕ ብር እንደሚከፈሉና ምንም ገቢ የሌላቸው ዜጎች ወጪንም መንግሥት እንደሚሸፍን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት የነበረው የክፍያ ስርዓት ሁሉም ዜጋ 1 ሺሕ 500 ብር ይክፈል የሚል እንደነበር በማስታወስም፤ በዚህ ዓመት አቅማቸውን ያገናዘበ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ይህም በዚህ ዓመት በተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ ይሕንን ማድረግ ያስፈለገው የመዋጮ ሁኔታው አቅምን ያገናዘበ የአከፋፈል ስርዓት እንዲከተል አዋጅ ላይ በመቀመጡ ነው ብለዋል፡፡ አዋጁ ሲዘጋጅም ይሁን ተግባራዊ ሲደረግም በጥናት ላይ ተመሰርቶ መሆኑን ተናግረዋል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ