ሕዳር 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣምና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ መፍትሄ ለማስቀመጥ፤ ከፈረንሳይ ኤምባሲ እና ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ መኖሩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጿል።

በዚህ ሂደት ምርቱን ከሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ 'አያዋጣም' በማለት እየዘጉ እንደሚገኙ፤ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን የሚገልጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ "ነገር ግን የተደራሽነትና የምርት ችግር አለ" ብለዋል።

በመሆኑም አቅርቦትና ፍላጎቱን ለማጣጣምና በኢንዱስትሪዎች በኩል ያለውን ተግዳሮት በማስተካከል ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከስርጭት ጋር በተያያዘ ምርቱ እንዲወደድ ለማድረግ አምራቾች መጋዘን ውስጥ እንዳይሸጥ የሚያስቀመጡበት አግባብ መኖሩን ያነሱ ሲሆን፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ይሰራበታል ብለዋል።

Post image

በሌላ በኩል ከዋጋ ውድነቱ አንፃር የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ በየአካባቢው ተደራሽ ቢሆን እንኳን፤ ከማህበረሰቡ አቅም በላይ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም መሠረታዊ የጤና ግብዓቶች ውስጥ እንዲካተት በማስቻል እና ከቫት ወይም ከታክስ ነፃ ሁኖ እንዲገባ በማድረግ በፋርማሲዎች አካባቢ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጥ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት አካባቢ እንደ ቅንጦት ምርት ተቆጥሮ ከ60 በመቶ በላይ ታክስ ይጣልበት እንደነበረ አስታውሰው፤ ከዛ በኋላም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎችም አጋር አካላት ጋር በመሆን የሚጣልበትን ታክስ ወደ 30 በመቶ ማውረዱን አንስተዋል።

በቅርብ ጊዜ በተሰራ ሥራ ደግሞ ወደ 10 በመቶ ወርዶ እንደሚገኝ የገለጹት መሪ ሥራአስፈፃሚው፤ ያም ሆኖ ግን ከኑሮ ውድነቱ አንፃር የዋጋ ግሽበቱ ስላለ ዋጋው አሁንም ድረስ የቀነሰበት አግባብ ባለመኖሩ ምርቱ በቅናሽ እና በተሻለ ተደራሽነት የሚመረትበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራበት ነው ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን በተለይም የሰብዓዊ ቀውስ በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ ሴቶች ተደራሽ ለማድረግ የድጋፍ ደብዳቤ በማፃፍ ሙሉ ለሙሉ ከታክስ ነፃ ሆኖ የሚገባበት እና የሚሰራጨብት አሰራር መኖሩን አስታውቀዋል።

በትምህርት ቤቶች ላይም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በስርዓተ ፆታ ክበቦች አማካኝነት ለተማሪዎች በነፃ እንደሚቀርብ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ