ሕዳር 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ውስጥ የሴት ልጅ ግርዛት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈፀም የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

ቅንጅቱ ባወጣው መረጃ 65 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለግርዛት አደጋ የተጋለጡ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል 34 በመቶ ያህሉ ለአካለ መጠን ሳይደርሱ ይዳራሉ ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ይህ ችግር እንዲባባስ ያደረጉትን ዐበይት ምክንያቶች ድርጊቱን በጥልቀት ሊያወግዝ የሚችል መዋቅራዊ አስገዳጅ ሕግ አለማውጣት ወይም የወጡ ሕጎችን በተገቢው መንገድ አለመተግበር ቀዳሚ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ከዚህም ባሻገር የቤተሰብ የግንዛቤ ማነስ፣ ድህነት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ከመጠን በላይ በባህል ማመን፣ እንዲሁም ግጭትና ጦርነት ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች ናቸው።

የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት ከሚፈጸምባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ድሬዳዋ እና አፋር ለአብነት እንደሚጠቀሱ ቅንጅቱ ለአሐዱ አስታውቋል።

የሴት ልጅ ግርዛት ለከፍተኛ ደም መፍሰስ እና ለሽንት ችግር፣ ለተዛባ የወር አበባ፣ ለኢንፌክሽን፣ እንዲሁም፤ በወሊድ ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ለጨቅላ ሕጻናት ሞት የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል።

የሴት ልጅ ግርዛት ላይ በዓለም ጤና ድርጅት የተካሔደ ጥናት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአውሮፓውያኑ 2025 ከ230 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች እና ሴቶች የሴት ልጅ ግርዛት እንደተፈፀመባቸው ያመለክታል።

ድርጊቱን በስፋት የፈፀሙት የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፤ ከእነዚህም መካከል በመካከለኛው ምሥራቅ አፍሪካና በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሽ ናቸው።

የሴት ልጅ ግርዛት በአብዛኛው የሚከናወነው ከጨቅላነታቸው ዕድሜ እስከ 15 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ባሉ ወጣት ልጃገረዶች ላይ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ