መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሰሞኑ ብዙ ሰዎችን እያጋጠመ ያለው ጠንከር ያለ ጉንፋን ከተለመደው በተለየ ቫይረስ እንዳልከሰተና እስከ ታኅሣሥ ወር አጋማሽ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፤ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን እያጠቃ ያለው ጉንፋን መሰል በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት እና ከዚህ ቀደም ከነበሩት ኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች የተለየ እንዳልሆነ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ለቫይረሱ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የፈጠረው መስከረም ወር ሰዎች በብዛት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት፣ በርካታ ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩበት እንዲሁም ቁጥራቸው የበዛ ተሳታፊዎች የሚታደሙባቸው የአደባባይ በዓላት የሚከወኑበት በመሆኑ ነው ሲሉ ዶ/ር መሳይ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም፤ የሰዎች የመከላከል አቅም መቀነስ ቫይረሱ ጉልበት እንዲያገኝ እና ሕመሙ እንዲበረታ አድርጎታል ብለዋል።
ብሔራዊ የኢንፍሉዌንዛ ማዕከል ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት አዲስ ዓይነት ቫይረስ አለመግባቱን ማረጋገጡን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቫይረሱ ስርጭት እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ ሊዘልቅ እንደሚችል ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ስለ ኢንፍሉዌንዛ እና ሌሎች ጉንፋን መሰል ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱ በሽታዎች ሰፋ ያሉ መረጃ እንደሚያቀርብ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ሕብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድ መክረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ