መስከረም 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የማካካሻ ወይም ሪሚዲያል ፈተና ወስደው ውጤት ያመጡ አምስት የሕግ ታራሚዎች ለመጀመረያ ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን የጂንካ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም አስታውቋል።
28 የሕግ ታራሚዎች በ2015 ዓ.ም የማካካሻ ትምህርታቸውን ወደ አርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም ተልከው ሲከታተሉ መቆየታቸውን የተቋሙ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ነሬሬ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በኋላም ለፈተና ከተቀመጡ 28 የሕግ ታራሚዎች ስድስት ታራሚዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባቸውን ውጤት ማምጣታቸውን የገለጹ ሲሆንለ ጫሞ ካንፓስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መመደባቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን ታራሚዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ትምርህታቸውን መቀጠል ባለመቻላቸው ወደ ማረሚያ ተቋሙ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል አንደኛው የእስር ጊዜውን አጠናቆ መፈታቱን አዛዡ ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ አምስት የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ተቋሙ የእርምት ጊዜያቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ታራሚዎች በዚህ ሁኔታ እንዳሉ በጂንካ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ የተመራ ልዑክ በተቋሙ ጉብኝት ማድረጉን ተከትሎ፤ ነገሮች መለወጣቸውን አዛዡ ገልጸዋል።
ስለሆነም ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ ሰሞኑን በተቋሙ ጉብኝት ባደረጉት ወቅት በሪሚዲያል ውጤት አምጥተው የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን መቀጠል ላልቻሉ አምስት የሕግ ታራሚዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንደሰጡ ተናግረዋል።
በቀጣይ የሕግ ታራሚዎች የመጀመሪያ ድግሪ ትምህርታቸውን በምን አይነት መንገድ መከታተል እንዳለባቸው ከዩንቨርስቲው ጋር መግባባት እንደሚደርስም አዛዡ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የጂንካ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ለአሐዱ የተናገሩት ምክትል ኮማንደር አስቻለው፤ በቅድመ መደበኛ ደረጃ የሚማሩት ከሕግ ታራሚዎች ጋር በተቋሙ የሚገኙ ሕጻናት እንደሆኑ ገልጸዋል።
ከአንደኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ያሉት ደግሞ በማረሚያ ተቋሙ በእርምት ላይ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ናቸው ብለዋል።
በዚህም መሠረት በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ700 በላይ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ተቋሙ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አምስት የሕግ ታራሚዎች ለመጀመረያ ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸው ተገለጸ
