ሕዳር 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትልና ጥራት የጎደለው የምግብ ዘይት ምርት ላይ እንደ 'ሃይድሮጂኔትድ' ያሉ ኬሚካሎችን በመጨመር፤ "ጥራት ያለው" በማስመሰል ለገበያ የሚያቀርቡ ሕገ-ወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
አንዳንድ አምራች ድርጅቶችና ነጋዴዎች ጥራት የጎደለው ምርታቸው ጥራት ካለው ምርት ጋር በመልክ እንዲመሳሰል ለምግብ ግብዓትነት እንዲውል ያልተፈቀደ ቀለም እንደሚጨምሩ "ደርሼበታለሁ" ነው ያለው ተቋሙ፡፡
ይህንን እና ይህንን መሰል ሕገ-ወጥ የወንጀል ተግባር ለማስቆም የተዘረጋው አዲሱ ሥርዓት፤ ምርቱ ከፋብሪካ ወጥቶ ለተጠቃሚው እስኪቀርብ ድረስ ያለውን የጥራት ሂደት ከሥር ከሥር የሚፈትሽና የሚያረጋግጥ መሆኑም ገልጿል።

የባለሥልጣኑ የእንስሳት ተዋጽኦ እና አልሚ ምግብ ዴስክ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ አዲሱ ሥርዓት ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ፤ ተመሳሳይ ተግባር የሚፈጽሙ ጥፉተኞች ከእኩይ ድርጊታቸው ተቆጥበዋል።
የቁጥጥር እና ክትትሉን ውጤታማነት የሚያሳየውም በአሁኑ ሰዓት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዘይት አምራቾች ደረጃቸውን የጠበቁ የምግብ ዘይት ምርቶች ለገበያ ማቅረባቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘው የአሰራር ስርዓት ድንገተኛ ፍተሻን፣ የላቦራቶሪ ምርመራን፣ የምርት ግብዓት ፍተሻን፣ የአመራረት ሂደትን እና መሰል ለጥራት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን ፈትሾ ማሳለፍን ያጠቃልላል ተብሏል።
ባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት ደህንነቱ ያልተረጋገጠ የምግብ ዘይት ለገበያ ባቀረቡና የብቃት ማረጋገጫ በሌላቸው ከ70 በላይ የምግብ ዘይት አምራች ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
የሕብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ እንዲህ ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ዜጎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለማጋለጥ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበሩም ኃላፊው አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ