የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2017 ዓ.ም የግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ አንድ ወሳኝ አዋጅ አጽድቋል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የሕግ ማዕቀፍ ነው።
በዚህም መሠረት አንጋፋው ተቋም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በመሆን አዲሱን የለውጥ መንገድ ጀምሯል።
ይህ የሽግግር ሂደት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረ ቢሆንም፤ በዚህ ብቻ የሚቆም እንዳልሆነ ተመላክቷል። ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በሂደት ይህንን አሰራር እንደሚተገብሩ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከሚገኙት በርካታ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል፤ የተወሰኑት ብቻ ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ይሸጋገራሉ ተብሎ ታቅዷል።
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንደገለጹት፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አስር ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው።

የዩኒቨርሲቲዎች የቀጣይ የሪፎርም የመጨረሻ መዳረሻም ይኸው ራስ ገዝ የመሆን ጉዳይ ነው። ፕሮፌሰሩ አክለውም፤ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ለዓመታት የቆየውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አሁን የተደረሰው የራስ ገዝነት ደረጃም የዚሁ የጥራት ማሻሻያ ጉዞ አንድ አካል ነው። በዚህ እቅድ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ከተካተቱት ዩኒቨርሲቲዎች መካከልም የባህርዳር፣ የጎንደር፣ የጅማ፣ የሀዋሳ፣ የአርባ ምንጭ እና የመቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል።
ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ደርግ ከንጉሡ ሲረከበው ነፃ ተቋም እንደነበር እናያለን። ይሁን እንጂ በ1969 ዓ.ም. ደርግ ሥልጣን ከያዘ ጥቂት ዓመታት በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን የሚል አዋጅ ታወጀ።
ይህንን ተከትሎም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮሚሽኑ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር እንዲገባ ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የተቋሙ አሠራር ተቀይሮና ነፃነቱ ተገደቦ መቆየቱን ታሪክ ያስታውሰናል።
አሁን ግን ከ75 ዓመታት በኋላ ይህ ታሪክ ተቀይሯል። 75 ዓመት ዕድሜ ያለው ይህ አንጋፋ ተቋም፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ በመመለስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቅቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ይህ ሥራ የመንግሥት የለውጥ ሥራ አንድ አካል መሆኑን በጽኑ ያምናሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አዋጁ በ2015 ዓ.ም. ከወጣ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝነት መንገድ ለመውሰድ በርካታ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በተደረገው የቅድመ ዝግጅት ሂደት ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያግዘውን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘጋጅቷል። ይህ ዕቅድ ከ2024 እስከ 2028 ድረስ ባሉት 5 ዓመታት ተቋሙን የሚመራበት ወሳኝ ሰነድ ነው። ዕቅዱን በማዘጋጀትም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሕግ ማዕቀፍ ነው። በተለይም የዩኒቨርሲቲውን የሴኔት ሕግ፣ አዲስ ከወጣው የራስ ገዝ አዋጅና ከማቋቋሚያ ደንቡ ጋር እንዲጣጣም የማድረግ ሥራ በልዩ ትኩረት ተሠርቷል።
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ከሚሰጧቸው በርካታ ዕድሎች መካከል አንዱና ዋነኛው፤ ተማሪዎችን በተመለከተ የሚኖራቸው ሥልጣን ነው። ተቋማቱ የራሳቸውን ተማሪዎች በራሳቸው መሥፈርት የመመልመል እና የመቀበል ሙሉ መብት ይኖራቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ነፃነት ያገኛሉ። የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር፣ የሰው ኃይል ምደባ፣ የቅጥር ሁኔታ እና የደመወዝ ስኬል የመወሰን ሥልጣን ይኖራቸዋል። በዚህም ምክንያት ነባሩን የሲቪል ሰርቪስ ሕግ መከተል አይጠበቅባቸውም።
ለራሳቸው በሚመችና ተወዳዳሪ በሚያደርጋቸው መልኩ እነዚህን ጉዳዮች እንዲያዘጋጁ አስተዳደራዊ ነፃነት እና ሥልጣን እንደሚያገኙ ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
ሌላው የራስ ገዝነት ትሩፋት ተብሎ የተገለጸው በአካዳሚክ ዘርፍ የሚታየው ነፃነት ነው። ተቋማቱ አዲስ የትምህርት ክፍል መክፈት ካስፈለጋቸው፣ ረዥም ቢሮክራሲ ውስጥ ሳያልፉ ራሳቸው መወሰን ይችላሉ። እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫቸውን መሠረት በማድረግ የጥናት እና ምርምር ዘርፎችን የመለየት መብት አላቸው። ከዚህም ባሻገር ከየትኛውም ውጫዊ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው መሥራት እንደሚያስችላቸው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ይህንን ነፃነት ተከትሎ የተቋሙን መዋቅር የማስተካከል ሥራ ተጀምሯል። ዩኒቨርሲቲው ወደዚህ አዲስ አሠራር ሲገባ፣ በፊት የነበሩት ወደ 658 የሚጠጉ የኃላፊነት ቦታዎች እጅግ የተለጠጡ እንደነበሩ ዶክተር ሳሙኤል ያስታውሳሉ።

ይህንን የተንዛዛ መዋቅር የማስተካከል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በተሠራው ሥራ የኃላፊነት ቦታዎችን ብዛት ወደ 440 ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል። ይህ እርምጃ ተቋሙን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው።
በብዙዎች ዘንድ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ የበጀት ጉዳይ ነው። ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማለት ከመንግሥት ምንም ዓይነት በጀት አይጠብቅም ማለት ነውን? ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ሳሙኤል ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ራስ ገዝ መሆን ማለት ከመንግሥት ሙሉ በሙሉ በጀት ይቋረጣል ማለት አይደለም። ነገር ግን የበጀት መጠኑ እና አሰጣጡ ሊለያይ እንደሚችል አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያቀደውን ስትራቴጂያዊ ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልገዋል። በ5 ዓመት ውስጥ ለታቀዱት ሥራዎች በአጠቃላይ 59 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። ይህ ማለት በዓመት በአማካይ 11 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ማለት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የዚህ ሁሉ ለውጥ መሠረታዊ ዓላማ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አቅም ማሳደግ ነው። ተቋማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ጥልቅ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት እና የምርምር ሥራ የሚካሄድባቸው ማዕከላት ሊሆኑ ይገባል።
የዳበረ ዕውቀት የሚገኝባቸው፣ የፈጠራ ሐሳብና ሥራ የሚስፋፋባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ታቅዷል። ተግባራቸውን በብቃት የሚያከናውኑ ተመራማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ሠራተኞችንና ተማሪዎችን ያቀፉ አድርጎ እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የገቢ ምንጮች በማስፋፋት አቅማቸውን ማጎልበት አለባቸው። ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ አገራዊ የልማት ትልሞችን ለማሳካት እንደሚያስችል ታምኖበታል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55(1) መሠረት ሆኖ ይህ የራስ ገዝነት አዋጅ ታውጇል። በዚህ መሠረትም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተከትለው እንደ ጎንደር፣ ሐረማያ እና ጅማ ያሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዙን መንገድ መጀመራቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ከሕግ ማዕቀፍ አንጻር ዶክተር ሳሙኤል ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከሕጎች ጋር በተያያዘ ከአዋጁ ጋር የተጣጣሙ ደንቦችና ፖሊሲዎች እየተዘጋጁ ነው። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆኑ ውስጣዊ ሕጎችን እንደሚያዘጋጅም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሴኔት ሕግ መሻሻሉን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ተቋሙ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአሠራር ነፃነት እንደሚፈልግም ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለው ቦታ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ተቋሙ ከተቋቋመበት ከታኅሣሥ 1943 ዓ.ም ጀምሮ በሰው ኃይል ልማት፣ በጥናትና ምርምር ዙሪያ የመሪነት ሚናውን እንደያዘ ይገኛል። አሁንም ቢሆን አቅሙን እያሰፋ ነው።
ከ10 ሺሕ በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ፈጥሯል። በጤናው ዘርፍም ቢሆን፤ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኩል በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ሕክምና ፈላጊዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ይህንን የመንግሥት አቅጣጫ ተፈጻሚ ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ሲገልጽ ቆይቷል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለተቋቋሙበት ዓላማ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይም በዋናነት የዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፋዊነት ላይ በፅኑ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ ከተቻለ የታለመውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የራስ ገዝነት ጉዞ አልጋ በአልጋ ብቻ አይደለም። የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ከመንግሥት በጀት የሚያስወጣቸው መሆኑ ስጋት ፈጥሯል።
ይህ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲዎቹ በጀታቸውን ለማግኘት ሲሉ ክፍያ መፈጸም የሚችሉ ተማሪዎችን ብቻ በመመልመል እና በመቀበል ላይ እንዲያተኩሩ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚለው ጉዳይ አሁንም በስጋትነት ይጠቀሳል።
በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ጉዳይ ያሳስባል። ይህ አካሄድ ድሆችን ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት ውጪ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉ ወገኖች፣ ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ