የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት (RRS) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከቀጠናው ውጪ ያሉ ሀገራትን ጨምሮ ከ34 ሀገራት የመጡ ስደተኞች ተቀብላ እየተስተናገደች መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ከሚቀበሉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ነች። ከሚገኙት ስደተኞች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን የመጡ ሲሆኑ፤ ይህም ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ቀጥሎም 33 በመቶ የሚሆኑት የሶማሊያ ሲሆኑ፣ የኤርትራ ስደተኞች ደግሞ 17 በመቶ እንደሚይዙ የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ኃላፊ ወይዘሮ ጣይባ ሐሰን ለቋሚ ኮሚቴው በሪፖርታቸው ወቅት ገልጸዋል።

አብዛኛው ስደተኛ ከደቡብ ሱዳን በመሆኑ፣ በርካታ ስደተኞችን በመቀበል የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ቁጥርን ይይዛል። ክልሉ ከ400 ሺሕ በላይ ስደተኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን፤ ቤንሻንጉል እና አፋር ደግሞ በተከታይነት በርካታ ስደተኞችን የሚቀበሉ ክልሎች መሆናቸውን ወይዘሮ ጣይባ አስረድተዋል።
በዋና መሥሪያ ቤቱ ደረጃ ሰባት የሚሆኑ ቅርንጫፎች ያሉት ተቋሙ፤ አዲስ አበባ እና መቐለን ጨምሮ በከተሞች ውስጥ ወደ 70 ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞችን እያስተናገደ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

ተቋሙ በዋና መሥሪያ ቤቱ ደረጃ ሰባት የሚሆኑ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ አዲስ አበባ እና መቀሌን ጨምሮ በከተማ 70 ሺሕ ስደተኞችን እያስተናገደ ይገኛል።
የፖሊሲ ማሻሻያ እና አዲስ የሕግ ማዕቀፍ
ወይዘሮ ጣይባ ሐሰን ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት፣ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የስደተኞች ምላሽን ማዕከል እንደሚያደርጉና በተለይም የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እና እንደ አሜሪካ ያሉት የውጭ ስደተኞችን በተመለከተ ፖሊሲያቸውን በተደጋጋሚ ጊዜ እየከለሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በመሆኑም፤ ኢትዮጵያም ጊዜውን የሚዋጅ አዲስ ፖሊሲ ማውጣት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያም ጊዜውን የሚዋጅ አዲስ ፖሊሲ ማውጣት ግድ የሚላት ጊዜ ላይ በመገኘቷ፤ አዲስ የፍልሰት ፖሊሲ ማዘጋጀቷን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በ2011 ዓ.ም. ቢቋቋምም ፖሊሲ እና ደንብ የወጣለት ግን ዘግይቶ በ2016 ዓ.ም. መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸው፤ በተጨማሪም ተቋሙ የሚያስፈልጉትን ወደ 20 የሚሆኑ የሥራ መመሪያዎችን የማውጣትና የማስተካከል ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልልን ሁኔታ በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እየተፈራረሰ በመሆኑ ስደተኞቹ ላይ በጥንቃቄ እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል።

"በተጨማሪም በጋምቤላ ክልል ያለውን ሁኔታ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለፅን ሲሆን፤ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እየተፈራረሰ በመሆኑ ስደተኞች ላይ በጥንቃቄ እየተሠራበት ነው" ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዲማ ነገዎ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ካሏት ስደተኞች ቁጥር አንጻር በዓለም ላይ ከለጋሾች እና አጋር ሀገራት ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ በመቀነሱ ከፍተኛ ጫና እንደተፈጠረ አንስተው፤ አማራጭ የድጋፍ ምንጮችን ለመፈለግ ተቋሙ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚያም ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቧል።
ከተነሱት ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል፡-
→ የሀገር ገጽታና ልመና ጉዳይ፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልል ከተሞች የውጭ ስደተኞች በስፋት በልመና ላይ መሰማራታቸው የሀገርን ገጽታ አያበላሽም ወይ? እየተሠራ ያለው የቁጥጥር ሥራ ምን ይመስላል?፣ ስደተኞቹ ወደ መጡበት ሀገር ለመመለስ የሚሠራው ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
→ የሰብዓዊነትና ግዴታ ሚዛን፤ ኢትዮጵያ የውጭ ስደተኞችን የምትቀበለው በሰብዓዊነት ነው ወይስ በዓለም አቀፍ ግዴታ ምክንያት ነው?
→ የሰው ኃብት አቅም፤ የስደተኞች ሥራን ውጤታማ ለማድረግ በሰለጠነ የሰው ኃብት አንፃርና የሰው ኃይሉ አቅም ምን ይመስላል?
→ ደኅንነት፤ በበጀት ዓመቱ ዋና ዋና ግቦች አንፃር አገልግሎቱ ከደኅንነት አንፃር የሠራው ሥራ ምን ያህል ውጤታማ የሚባል ነው?
በተጨማሪም ስደተኞቹ ወደ መጡበት ሀገር ለመመለስ የሚሰራው ሥራ ምን ይመስላል? እንዲሁም ኢትዮጵያ የውጭ ስደተኞችን የምትቀበለው በሰብዓዊነት ነው ወይንስ በዓለም አቀፍ ግዴታ ነው? የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አገልግሎቱ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ምላሽ፤ በዋናነት በውጪ ሀገር ስደተኞች ላይ ትኩረት አድርጎ ከመሥራቱ አኳያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስረድቷል። ደንቡ ዘግይቶ የወጣ ቢሆንም፤ በተቻለ መጠን ሰፋ ያለ ተቋማዊ ለውጦች መከናወናቸው ተነስቷል።
ወይዘሮ ጣይባ ሐሰን በሀገሪቱ የፍልሰት ሁኔታ እየተወሳሰበ መምጣቱን ያስረዱ ሲሆን፤ በተለይም ሕገ-ወጥ ስደት እየተበራከተ መምጣቱን ተናግረዋል።
በከተማ ውስጥ ስላሉ ያልተመዘገቡ ስደተኞች አስመልክተው ሲያስረዱም፤ ድንበር አቋርጦም ሆነ በአየር የገባውን ስደተኛ ሁሉንም መመዝገብ እንደማይቻል ገልጸዋል።
በከተማ ውስጥ ያሉ ያልተመዘገቡ ስደተኞች በሚመለከት ያስረዱት ኃላፊዋ፤ "በድንበር አቋርጦም ሆነ በአየር የገባውን ስደተኛ ሁሉም መመዝገብ አንችልም" ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከአቅምም ሆነ ከደህንነት አንፃር ተገቢ ሊሆን የሚችል ጉዳይ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የበጀት ምንጮችን ለማስፋት ሰፊ ሥራዎች ከልማት አጋሮች የዓለም ባንክ (World Bank)፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ (African Development Bank) እና እንደ ኳታር ካሉ የገልፍ ሀገራት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ ሥጋቶችን ከመከላከል አንፃር፤ ስደተኞች በማንኛውም ወንጀል እንዳይሳተፉ በቋሚነት የማስተማር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በተጨማሪም የጸጥታ ዳሰሳ ጥናቶች እንደሚሠሩ ተገልጿል። በዚህም ጎላ ያለ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ