ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተው እና ምንነቱ ለማረጋገጥ የዘረመል ምርመራ ሲካሄድበት የቆየው ሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ መንስኤ ማርበርግ ቫይረስ (Marburg Virus) ስለመሆኑ መረጋገጡን፤ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው ይታወቃል።
በወቅታዊ የጤና ሁኔታ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ዛሬ ሕዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ሕዳር 3 ቀን በሽታው ይፉ ከተደረገ በኋላ በ17 ሰዎች ላይ በተወሰደው ናሙና በተረጋገጠ ምርመራ በማርበርግ ቫይረስ 3 የሞቱ ሰዎች እንዲሁም በማርበርግ የተጠረጠሩና በላብራቶሪ ያልተረጋገጠ 3 ሰዎች፤ በአጠቃላይ 6 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ሲሉ ገልጸዋል።
ምርመራው ከተደረገላቸው ሰዎች ቀሪዎቹ ነፃ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር በኩሉ "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከፍተኛ የዝግጅት እና የቅንጅት ሥራዎችን እየሰራን ነው" ያሉት ሚንስትሯ፤ ወደ ክልሎች ድጋፍ የመላክና ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የተገናኟቸው ሰዎች የመለየት ሥራ እንደተሰራ አንስተዋል።
ሕብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና ከሌሎች ሕመሞች የሚለይበትን መንገድ ማወቅ ይገባል ያሉም ሲሆን፤ ምልክቱ ከታየባቸው ሰዎች ጋር የሚደረግ ንክኪ መተላለፊያ መንገዱ ነው ብለዋል።
ማርበርግ ቫይረስ በትንፋሽ የሚተላለፍ አለመሆኑና ለመከላከል ንክኪን መቀነስ እጅን መታጠብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት በዚህ በሽታ የተያዙ ታማሚዎች አለመኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ፤ ይህ ማለት የሚያዘናጋ አለመሆኑንና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እና ባለበት እንዲቆም ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር የመጀመሪያው መንገድ መከላከል ሲሆን፤ ምልክቶች የታዩባቸውን ሰዎች ሕክምና ለመስጠት ፈሳሽን የመተካት እና እንደ ሕመሙ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ነገር ግን ለዚህ ይሆናል ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠለት መድሃኒት አለመኖሩን ተናግረዋል።
በተለያዩ ሀገራት በሙከራ ደረጃ ላይ ያሉ መድሃኒቶችና ክትባቶች መኖራቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ማለፍ ያለባቸው ሂደቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የማርበርግ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ሀገር በአውሮፓውያኑ 1967 መታየቱን አስታውሰዋል።
ከዛ በኋላ በ12 ሀገራት ላይ የታየ ሲሆን፤ በአፍሪካ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ጋና፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ላይ መታየቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መከሰቱንም ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል።
ሕብረሰተቡ መረጃዎችን እና የጥንቃቄ መንገዶችን ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መከታተል እንዳለበትም አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ