ሕዳር 8/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በእስራኤል ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት እና በተቀበረበት ጎሎጎታ አካባቢ ያላት የቤተክርስተቲያን ይዞታ ላይ፤ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የገባችበት የባለቤትነት ውዝግብ እስካሁን አለመፈታቱን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
አምባሲው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእየሩሳሌም፣ በቤተልሔም እንዲሁም በኢያሪኮ ከተሞች አብያተ ቤተክርስቲያናት እንዳላት የገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም በ6ቱ ቀን ጦርነት ወቅት ፈርሶ የነበረውን የሥላሴ ቤተክርስቲያን በዮርዳኖስ አካባቢ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በዚህም በአጠቃላይ ወደ 7 የሚደርሱ የኢትዮጵያ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት በሀገሪቱ እንደሚገኙ ለአሐዱ ሬዲዮ የገለጹት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ፤ ኢትዮጵያ በእስራኤል ውስጥ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ሕንጻ ያላት ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ቤተክርስቲያናት መካከል በጎሎጎታ የሚገኘው ቤተክርስቲያን ከ'ባለቤትነት ይገባኛል' ጋር በተያያዘ የተገባው ውዝግብ ከፍተኛ ጭቅጭቅ እያስከተለ መቀጠሉ ነው የገለጹት፡፡
አክለውም፤ "በአሁኑ ሰዓት በጎሎጎታ ውስጥ የሚገኙት መድኃኒዓለምና ሚካዔል ቤተክርስትያናት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየተገለገለች ቢሆንም የቦታ ማረጋገጫ ካርታ የለንም" ብለዋል፡፡
"ግብጾች ቦታውን አልወሰዱትም፡፡ እኛም መንፈሳዊ አገልግሎታችንን አላቋረጥንም" ያሉት አምባሳደሩ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ለማሳደስ፣ የመብራትና የውሃ የመሳሰሉትን ከማዘጋጃ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ግን አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያኑ የሚገኝ አንድ ዛፍ በአንዲት አነስተኛ ቤት ላይ ወድቆ የደረሰን ውድመት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እንዲታደስ መደረጉን አንስተው፤ "አደጋ የደረሰበት ቤት ሲታደስ የግብጽ ኮፕቲኮችን ይሁንታ አልጠየቅንም፡፡ ይህም ኮፕቲኮቹን ሊያስከፋ ይችላል" ብለዋል፡፡
ነገር ግን ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በእስራኤል በመገኘት ገዳሙን በመጎብኘት መነኮሳቱ ያለውን ችግር አስረድተዋቸዋል፤ ሚኒስትሩም ይህንን የመነኮሳቱን ጥያቄ በመያዝ ለእስራኤሉ አቻቸው አስደርተው በዚያ መሰረት ቤቱ ሊታደስ ችሏል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ቤተክርስቲያናቱ የኤሌትሪክ አገልግሎት ብታገኝም በቂ ኃይል እንደሌለው አምባሳደር ተስፋዬ የገለጹም ሲሆን፤ ጉዳዩ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ተይዞ ኃይሉ ከፍ የሚልበትን ሁኔታ ለመፈለግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ደረጃ በደረጃ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገልጸው፤ "ይህ ወደ 300 ዓመት የቆየ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም በአጭር ጊዜ መፍትሔ ላያገኝ ይችላል፡፡ ቀስ በቀስ ግን መፍትሄ የሚያገኝበት ሁኔታ ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል፡፡
"በእስራኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት ተከታዮች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ በየጊዜው እየጨመረ ነው" ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ በአንፃሩ የግብጽ ኮፕቲኮችን ቁጥር ደግሞ እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ኢተዮጵያ ቤተልሄም ላይ ትልቅ ቤተክርስቲያን እንዳላት ያነሱም ሲሆን፤ ካሉት ቤተክርሲቲያኖች የባለቤትነት ውዝግብ እና ሌሎች ችግሮች ያሉበት በጎሎጎታ የሚገኘው ቤተክርስቲያን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በእስራኤል ውስጥ ስታተስ ኮ (states quo) የተሰኘ አሰራር ወይንም ሕግ መኖሩን ያነሱም ሲሆን፤ አሰራሩ "ሁሉም ነገር ባለበት ይቆይ" የሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስለሆነም ይህንን ሕግ የእስራኤል መንግሥት መጣስ እንደማይፈልግ በማንሳት፤ "ይህንን ጠብቆ ከሀገሪቱ ማዘጋጃ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ደረጃ በደረጃ እየሰራን ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ይህ ስታተስ ኮ የሚባለውና 'ሁሉም ነገር ባለበት ረግቶ ይቆይ' የሚለው የእስራኤል አሰራር በቀላሉ የሚታይ አይደለም" ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ ሕጉ ከሐይማኖታዊ አንጻር ብቻ ሳሆን ከፖለቲካ እና ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር ሁሉ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ግብፅና እስራኤል ያላቸው ግንኙነት፣ የኢትዮጵያን እና እስራኤል ያላቸው ግንኙነት እንዲሁም፤ እስራኤልና ግብጽ ያላቸው ግንኙነት የየራሳቸው ተጽዕኖ ይታያል፡፡ ስለሆነም ሂደቱ በዚህ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በጎሎጎታ ያለውን ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት ኮሚቴ ተቋቋሞ እንዲሁም የሀገሪቱን ሕግ በደንብ የሚያውቅ ጠበቃ ተቀጥሮ ሲሰራበት እንደነበር ያስታወሱም ሲሆን፤ ነገር ግን ሂደቱ ውጤት ሳመጣበት መቅረቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደ ባለቤት ማዘጋጃ ቤት የሚሰጠው የባለቤትነት ማረጋገጫ ሳይኖር ቅዳሴ እንደሚከናወንና መነኮሳቱ በቅጥሩ ውስጥ እንደሚኖሩ አብራርተዋል፡፡
"የእስራኤል መንግሥት የሁለቱንም ሀገራት ፍላጎት ይጠብቃል" ይሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ "በአንድ በኩል እኛን አያስወጣም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ እናንተ ነውና ብሎ ካርታውን አይሰጠንም" ብለዋል፡፡
"በዚህም መሠረት የምዕመናን ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱ፣ በቦታው ላይ እኛም መቆየታችን እና አለመልቀቃችን፣ ጥያቄን አሁንም አለማቋረጣችን እንዲሁም፤ በሀገሪቱ የሐይማኖት ሚኒስትር መኖሩ ውጤት ያለው ነገር እንድናገኝ ያስችለናል፡፡ ነገር ግን መቼ ነው? የሚባለውን ነገር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም" ብለዋል፡፡
አክለውም በእስራኤል ሲካሄዱ የነበሩ ሲምፖዚየሞች እንዲሁም የምሁራኖች ጥናታዊ ወረቀት የሚያቀርቡባቸውት መድረኮች በቀጣይም እንደሚከናወኑ ገልጸው፤ እነዚህ ሥራዎች ግንዛቤ ለመጨመር እንዲሁም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች በደንብ እንዲያዙ ለማድረግ እንደሚረዱ አስረድተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በእስራኤል ጎልጎታ በሚገኘው ቤተክርስቲያን ላይ ግብጽ እና ኢትዮጵያ የገቡበት የባለቤት ውዝግብ እንዳልተፈታ ተገለጸ
ኢትዮጵያ እስራኤል ውስጥ ሕንጻ እና አብያተ ክርስቲያናት ያሏት ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ናት ተብሏል